የኢትዮጵያና ካናዳ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው

63
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2012 የካናዳ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢትዮጵያ አቻዎቻቸው በጋራ መስራት የሚችሉባቸው ጉዳዮችን ለመለየት ያለመ ውይይት ዛሬ ተደርጓል። በውይይቱም ከካናዳ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ምሁራን በኢትዮጵያ ካሉ የግልና የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሬፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከተቋቋመ ጀምሮ የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት እንዲሁም ሀገራዊ የሳይንስ ራዕዮችን ለማሳካት እየሰራ ነው። በቅርቡም በኢትዮጵያ ያሉ ዲፕሎማቶችን በመሰብሰብ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የወደፊት አቅጣጫዎችንና ተቋማዊ ትስስሮችን እንዲሁም እንደ ሀገር ልንሰራባቸውና በጋራ ልንከውናቸው የሚገቡ ተግባራትን አሳውቀናቸዋል ነው ያሉት። በወቅቱም ከካናዳ አምባሳደር ጋር ግንኙነት መፈጠሩን ጠቅሰው በአምባሳደሩ ከተላኩ ባለሙያዎች ጋርም ውይይት መደረጉንና የዛሬው መድረክም የእነዚህ ውይይቶች ውጤት መሆኑን አስረድተዋል። ካናዳ የስመጥር ዩኒቨርሲቲዎች መገኛ መሆኗና የሳይንስ መሰረቷም የሚደነቅ መሆኑን የገለፁት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ የሀገሪቷ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስርዓትም የጠነከረና ከኢንዲስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስርም ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል። በሀገሪቷ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከሚመረቁ ሰልጣኞች 95 በመቶ ያህሉ በ6 ወር ውስጥ ስራ ማግኘት መቻላቸውን በማሳያነት በመጥቀስ። "ኢትዮጵያ ለካናዳ ልትሰጥ የምትችለው በርካታ ነገር አላት" ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ በሀገሪቷ ተቋማት ውስጥ ያሉ በርካታ ኃብቶች መኖራቸውንን አስረድተዋል። በሀገሪቷ ያሉ የተለያዩ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሃብቶች መኖራቸው ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናት አጀንዳ እንደሚሆን በማከል። የካናዳ ምሁራን በኢትዮጵያ ፀጋዎች ላይ ከሀገሪቷ ምሁራን ጋር አብረው መስራታቸው ለሀገራቱ ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምም የሚሆን እውቀትና ሀብት እንዲያመነጩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ እንዲሆን በተገቢው መልኩ መመራት እንዳለበት በማከል። ካናዳና ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብረው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር አንቴኒ ቼቬየር ናቸው። በትምህርቱ ዘርፍ ላይም እየተደረገ ያለውን ለውጥ ካናዳ እየደገፈች መሆኗን ገልፀው የሀገሪቷ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን የምንደግፍበት መርሃ ግብር አለንም ብለዋል። ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለዓመታት በትብብር እየሰራን ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ በተለይም በጤናና በተፈጥሮ ሃብት ላይ በቀጣይም ያሉ ግንኙነቶችን በማጠናከርና ዘላቂ በማድረገ ይሰራል ነው ያሉት። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በበኩላቸው ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር መስራት በትምህርትና በምርምርም ትልቅ ልምድ የሚያገኙበትና የትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ክፍተት ለሙላት የሚያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1956 ሲሆን ካናዳ በኢትዮጵያ ኢምባሲዋን የከፈተችው በ1957 ኢትዮጵያ ደግሞ በካናዳ ኢምባሲዋን የከፈተችው በ1962 ነበር። በኢትዮጵያ 50 ዩኒቨርሲቲዎች፣ 229 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም 1ሺህ 622 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ይገኛሉ። በሀገሪቷ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግብአት፣ የአቅም፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም