አል በሺር ለአይ ሲ ሲ ተላልፈው ቢሰጡ እንደማይቃወም የሱዳን የነጻንትና የለውጥ ኃይሎች ቡድን አስታወቀ

51

ኢዜአ፤ ጥቅምት 24/2012 የቀድሞ ፕሬዚዳንት  ኦማር አል በሺር በዳርፉር እልቂት ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) ተላልፈው ቢሰጡ እንደማይቃወም የሱዳን የተቃዋሚዎች ቡድን አስታወቀ።

የቡድኑ መሪ ኢብራሂም አል ሼይክ ለሪፖርተሮች እንዳሉት “ሁሉም የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎችም በጉዳዩ ላይ ተስማምተዋል።”

አል በሺር በአሁኑ ጊዜ በካርቱም በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ሲሆኑ በሱዳን መንግሥትም የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር በወታደራዊ ኃይሉ ከስልጣን የወረዱት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሺር፤  ሀገሪቱን ከፈረንጆቹ 1989 ጀምሮ ለሦስት አስርት ዓመታት ገዝተዋል።

አል በሺር በምዕራባዊቷ ዳርፉር ክልል ለተፈፀመው እልቂት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የጦር ወንጀል እና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ ያደረጉ ግጭቶችን በመፍጠር ክስ ተላልፈው እንዲሰጡት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጠይቋል።

አል በሺር ከስልጣን እንደተባረሩ፥ በጊዜያዊነት ሱዳንን ሲያስተዳድሩ የሰነበቱት የሀገሪቱ የጦር ጀኔራሎች የቀድሞ ፕሬዚዳንቱን ለአይ ሲ ሲ አሳልፎ መስጠትን ተቃውመዋል።

ሱዳን ካለፈው ነሐሴ ወር ወዲህ በወታደራዊ እና በሲቪል ኃይሎች ጥምር ጊዜያዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት እየተዳደረች ነው።

አል በሺር ለአይ ሲ ሲ ተላልፈው እንዲሰጡና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ከተፈለገ የሽግግር ምክር ቤቱ መስማማት አለበት።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ትናንት በካርቱምና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎችን አድርገዋል።

በተቃውሞ ሰለፉም በፈረንጆቹ ባለፈው ሰኔ 3 ቀን ከወታደራዊ ዋና መስሪያ ቤቱ አቅራቢያ ለተቃውሞ የተቀመጡ ሰዎችን ለመበተን በተወሰደው እርምጃ የት እንደገቡ የማይታወቁ ዜጎች ጉዳይ ላይ የተጀመረው ምርመራ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

እንደ ተቃዋሚዎቹ ከሆነ 128 ሰዎች በወቅቱ የተገደሉ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጠፍተዋል፤ ባለስልጣናት በበኩላቸው የሟቾችን ቁጥር 87 ብቻ ናቸው ብለዋል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም