የግብርና ምርምር ማዕከሉ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች የግብአት ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ነው

157
ጥቅምት 24/2012  የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገጥማቸውን የግብዓት ችግሮች ለመቅረፍ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ። አርሶ አደሮች ከምርምር ማእከሉ ተቀብለው ያለሙትን የበቆሎ ዝርያ ለመገምገም በሰሜን አቸፈርና በሜጫ ወረዳዎች ትናንት የመስክ ጉብኝት ተካሐረዷል ። የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላየ ተክለወልድ በመስክ ጉብኝቱ ላይ እንደተናገሩት  ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የሚለቀቁ ምርጥ የሰብል ዝርያዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በስፋት በማባዛት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ክልሉ ለሀገራዊ የግብርና ምርት የ35 በመቶ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልፀው ኢንስቲትዩቱ  በስሩ በሚገኙ ሰባት  የሚርምር ማዕከላት አዳዲስ ቴክኖሎጂን በማፍለቅና በማላመድ ለምርታማነት ማደግ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን አስረድተዋል ። ከፌዴራልና በከልል የግብርና ምርምር ተቋማት የሚለቀቁ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ፣ ፍላጎት በመፍጠር፣ በማባዛትና በማሰራጨት ለምርታማነት እድገቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ። በመገንባት ላይ የሚገኘው የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዓመት 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ በግብዓትነት የሚጠቀም በመሆኑ ግብዓቱን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ። በመሆኑም በምርምር የሚለቀቁና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የበቆሎ ዝርያዎችን በማቅረብ አርሶ አደሩ በስፋት በማባዛትና በማልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በምርምር ማዕከላቱ አማካኝነት እየተሰራ ነው ። በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የበቆሎ ተመራማሪ አቶ መልካሙ እርቅይሁን በበኩላቸው ማዕከሉ በሰሜን አቸፈርና በሜጫ ወረዳዎች 34 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ቢኤች 546 የተባለ የበቆሎ ዝርያ እያባዛ ይገኛል። በ10 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በቅድመ ማስፋት እየተባዛ የሚገኘው የድቃይ በቆሎ ዝርያ በሔክታር እስከ 115 ኩንታል ድረስ ምርት የሚሰጥ ነው ። ይህንኑ ዝርያ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች ለማስፋት የመስክ ጉብኝቱ ምርታማነቱን ለማስተዋወቅ ጭምር መዘጋጀቱን አስረድተዋል ። አዲሱ የበቆሎ ዝርያ ቀደም ሲል ተለቀው አርሶ አደሩ ሲጠቀምባቸው ከቆዩት ቢኤች 540 እና 560 ዝርያዎች ጋር ሲነፃፀር በምርታማነቱ ከ10 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል ። የበቆሎ ዝርያው የኬክ መስሪያን ጨምሮ በተለያየ መልክ ለምግብነት በመዋል ተመራጭ ከመሆኑም በላይ በዋናነት ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ተፈላጊ መሆኑንም ተመራማሪው አስረድተዋል። አሁን እየተዋወቀ የሚገኘውን የበቆሎ ዝርያ በቀጣይ ዘር አባዢ ተቋማትና ድርጅቶች በስፋት አባዝተው ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በሰሜን አቸፈር ወረዳ የሊበን ዳንጉራ ቀበሌ አርሶ አደር ላቀ ቢተው በሰጡት አስተያየት አዲሱን ቢኤች 546 የበቆሎ ዝርያ በኩታ ገጠም እርሻ በግማሽ ሄክታር መሬት ሞክረውት ውጤታማ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። በግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ታግዘን መሬቱን እስከ አምስት ጊዜ ደጋግመን በማረስ በማልማታችን አሁን ላይ የፍሬ አያያዙን ሲያዩት ከ30 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በቀጣይ በስፋት ዘሩን በማባዛት ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እደሚሰሩም አስረድተዋል።   የበቆሎው የምርት አያያዝ ከዚህ በፊት ከሚጠቀሙባቸው የተሻለ በመሆኑ ዘሩ በቀጣይ በስፋት ሊቀርብላቸው እንደሚገባ የጠየቁት ደግሞ በመስክ በዓሉ የተገኙት የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ወይዘሮ ወጤ መልሴ ናቸው።   የክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን አቢታ በበኩላቸው ለቆሎ ምርት ተስማሚ በሆኑ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ዘሩን አባዝቶ ለማቅረብ በኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩ እንደሚሰራ  ገልጸዋል።   በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በቅድመ ማስፋት ለአርሶ አደሩ እየተዋወቀ የሚገኘው የበቆሎ ዝርያ ከሊሙ የበቆሎ ዝርያ ጋር ተመሳሳይ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው ተረጋግጧል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም