በሀብሩ ወረዳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ማጣት ሊዘጋ ነው

61
ወልድያ ኢዜአ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በሀብሩ ወረዳ የተገነባው አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ማጣት ምክንያት ሊዘጋ መቃረቡን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ገለፀ ። ትምህርት ቤቱ እንዳይዘጋ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በመፍትሔው ዙሪያ እየመከሩ ነው ተብሏል ። የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸጋው አገሸን እንደገለፁት በሀብሩ ወረዳ በ5 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ በ2009 ዓም ስራ የጀመረው የአረሪት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ማጣት ምክንያት ትርጉም ያለው አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበታል ። በአካባቢው እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምሩ 7 መጋቢ ትምህርት ቤቶች ታሳቢ በማድረግ የተከፈተ ቢሆንም ህብረተሰቡ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ባለመላኩ ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ አስረድተዋል ። ትምህርት ቤቱ ከ400 በላይ የ9ኛና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር አቅም ቢኖረውም ዘንድሮ የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 34 ብቻ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል ። ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት የማይልክ ከሆነ ከወጪ አንፃር መንግስትን ለኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ ትምህርት ቤቱ ሊዘጋ እንደሚችል የመምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል ። ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትምህርት ቤቱ እንዳይዘጋ ከፈለጉ የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው በየቤታቸው የተቀመጡ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ሸጋው አሳስበዋል ። የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ፈንታቢል ይመር እንዳሉት ከሆነ ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቱ እንዲልኩ ተደጋጋሚ ቅስቀሳ ቢደረግም ላለፉት ሶስት ዓመታት በአማካይ ተመዝግበው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ቁጥር ከ20 አይበልጡም ። ሰባቱ መጋቢ ትምህርት ቤቶች ባለፈው ዓመት በ8ኛ ክፍል ካስፈተኑዋቸው ተማሪዎች መካከል 109 ተማሪዎች ወደ 9ኛ ክፍል ቢያልፉም  85 ተማሪዎች በቤተሰብ ተፅእኖ ምክንያት እቤት ውስጥ መቅረታቸውን ርእሰ መምህሩ በማሳያነት ገልፀዋል ። የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ህብረተሰቡ የትምህርትን ጥቅም አለመረዳት ፣ ከዘላቂ ጥቅም ይልቅ ጊዜአዊ የልጆቹ ጉልበት መፈለግ ፣ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ከተማሩ አረብ አገር ሔደው ቤተሰቦቻቸውን ይርዱ የሚሉና ያለ ዕድሜ ጋብቻ በአካባቢው ሙሉ በሙሉ አለመወገዱ መሆኑን አስረድተዋል ። የሀብሩ ወረዳ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ጣውነህ በበኩላቸው የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ከህዝቡና ከቀበሌ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሔዶ ነበር ። ሆኖም ግን በተላይ ከትምህርት ቤቱ ራቅ ብለው የሚገኙ ወላጆች በመንገድ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ትንኮሳ በመፍራት ሴት ልጆቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል ። በትምህርት ቤቱ የ9ኛ ክፍል ተማሪ አህመድ አወል በሰጠው አስተያየት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው በቤታቸው መቅረታቸውን ገልፆ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን መዳር ወንዶቹን ደግሞ ወደ አረብ አገር መላክ መምረጣቸውን ችግሩ ፈታኝ አድርጎታል ብሏል ። የ10ኛ ክፍል ተማሪ ጀማል ሁሴን በበኩሉ በቤተሰብ ግንዛቤ ማነስ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን በመግለፅ ተማሪዎቹ የእኛን አርአያ ተከትለው ቤተሰቦቻቸውን በማሳመን እንዲቀላቀሉን ጥሪያችንን እናቀርባለን የሚል አስተያየት ሰጥቷል ። ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ካልቻሉ የትምህርት ቤቱ ዕጣ ፈንታ መዘጋት መሆኑን በውይይት መድረኩ ላይ ተገልፇል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም