የህዝቦችን የቆየ የአንድነት ታሪክ የሚሸረሽሩ ጉዳዮችን ለመከላከል የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው

69
ጥቅምት 22/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች የዳበረ የአብሮነት ታሪክ በመሰረተ ቢስ ትርክት እንዳይሸረሸር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች  ህዝቡን በማስተማር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገለፁ። "አማራና -ኪነጥበብ" በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በውይይቱ እንዳሉት ላለፉት አመታት የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ሙያው በሚፈልገው ልክ እንዲሰራ ባለመደረጉ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። በማህበራዊ፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚው  ዘርፍ በሚከወን እንቅስቃሴ ኪነ-ጥበብ ያልታከለበት ስራ "ጨው የሌለበት ወጥ እንደማለት ነው።" ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ሀገር ላለፉት አመታት  የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ያገለለና ኪነ-ጥበብን ለፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ ስራ ሲከወን መቆየቱንም አብራርተዋል። በተለይ እንደ አማራ ክልል ከኢትዮጵያ አልፈው በተለያዩ ሀገራት አንቱታን ያተረፉ  የጥበብ ባለሙያዎች ቢኖሩም ክልሉን በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማገዝ በኩል ሰፊ ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የ ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የፖለቲካው ሁኔታ አላሰራ ብሎ መቆየቱን ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ ግን የክልሉ መንግስት የ ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ለማገዝና  ሙያቸውን ለመጠቀም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል። "የተጠናከረ ክልልና የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትኖር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሙያ ነፃነታቸው እንደተጠበቆ ሆኖ ለሃገርና ለህዝብ በሚጠቅም መንግድ መስራት እንዳለባቸው አብራትዋል። የአማራ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሁኖ ኢትዮጵያን ጠበቆ ማቆየቱን አስታውሰው፤ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲስተካከሉ የኪነጥበብ ዘርፉን በዋናነት መጠቀም ይገባል። ልማትን ለማፋጠንና ሰላምን ለመሰበክ ኪነ-ጥበብ ትልቅ ድርሻ ቢኖራትም  ኪነ-ጥበብ   በፖለቲከኞች ተውጣ ቆይታለች ያለው ደግሞ ድምጻዊ  አሰማኸኝ በለው ነው። የኪነ-ጥበብ  ባለሙያው ሙያው በሚጠየቀው ነጻነት  ልክ ገለልተኛ ሁኖ ስራውን እንዲከውን ቢደረግ አሁን እንደ ሀገር የገጠመው የሰላም ችግር ሊከሰት አይችልም ብለዋል። "ነገር  ግን ኪነ-ጥበብ  በፖለቲከኞች ተገልላ ቆይታለች በመሆኑም እንደ ሀገር የ ኪነ-ጥበብ ባለሙያው መስራት ያለበትን ያክል አልሰራም" ብለዋል። የአማራ ክልል መንግስት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ሙያቸውን በተገቢው ሁኔታ  እንዲጠቀሙበት  የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ሊያስመሰግነው እንደሚገባም ጠቁመዋል። ጥበበኛ ዘር፣ ሀይማኖትና ፖለቲካ ውግንና  የለውም ያለው  ደግሞ ድምጻዊና ተዋናይ ዝናቡ ገብረ ሥላሴ  ነው። ዘረኛና  የፖለቲካ ውግንናን የሚያራምድ  የኪነ-ጥበብ ሰው ጥበበኛ ሳይሆን የኪነ-ጥበብ ጠላት ነው ሲሉም ገልፀዋል። ሙያው በሚፈቅደው መንገድ ለመስራት ባለፉት አመታት ፖለቲካዊ ችግሮች ተብትበው ይዘውት መቆየቱንና አሁን መንግስት ለዘረፉ ነጻነትን እየሰጠ ስለሆነ ሙያውን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቃል ብሏል። ለሁለት ቀንናት በሚቆየው የውይይት መድረክ  የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ድምጻዊያን፣ ደራሲያን፣ተዋንያንና የልይ ልዩ የኪነ-ጥበብ ተሰጥኦ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም