በምዕራብ ሐረርጌ የአንበጣ መንጋ ከ1ሺህ 100 ሄክታር በላይ የነበረ ሰብል አወደመ

74

ጭሮ ጥቅምት 22 ቀን 2012 በምዕራብ ሐረርጌ ዞን አራት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከ1ሺህ 100ሄክታር በላይ የነበረ ሰብል ማውደሙን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ገለጸ።

መንጋውን ለመከላከል ከአጎራባች ክልልች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

የመምሪያው  ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን መሐመድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት መንጋው ጉዳት ያደረሰው ካለፈው ወር ጀምሮ በአንድ ሺህ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ  ነው።

መንጋው በዶባ ፣ በጡሎ ፣ በሚኤሶና በጭሮ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 45 ቀበሌዎች ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

መንጋው እስካሁን ከ12ሺህ 500 በላይ ሄክታር ላይ ጉዳት ማድረሱን ያስረዱት ምክትል ኃላፊው፣ወደ ዞኑ ሌሎች ወረዳዎች እንዳይዛመት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች ጋር በመቀናጀት በባህላዊና ዘመናዊ መንገዶች ለመከላከል ጥረት መደረጉን አቶ ሁሴን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ሰብሉን ከአደጋ እንዲያድን  ጠይቀዋል።

የፌዴራል መንግሥት በጀትና መንጋውን የሚከላኩበው መሣሪያዎች እገዛ  በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።

በዞኑ በ2011/12 ምርት ዘመን 268ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም