ሰሊጥን በኩታገጠም ማሳ በመስመር በመዝራታችን ምርታማነታችን አድጓል----የሁመራ ወረዳ አርሶ አደሮች

107

ሁመራ (ኢዜአ) ጥቅምት 22 ቀን 2012 በትግራይ ክልል ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታገጠም ማሳ ላይ ሰሊጥን በመስመር የዘሩ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ማሳደጋቸውን ገለጹ።

በወረዳው በሦስት ቀበሌዎች በ1ሺህ 200 ሄክታር ኩታገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ለሙከራ የተካሄደ የሰሊጥ ልማት በመስክ ተጎብኝቷል።

በወረዳው አደባይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር  ታደሰ ፍሰሀ በወቅቱ እንደገለጹት በመኽር ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ በኩታ ገጠም ማሳ በመስመር ከዘሩት ሰሊጥ 12 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።

ያገኙት ምርት መጠን ከዚህ ቀደም በተለመዶ ይዘሩት ከነበረው በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

"ባለሞያዎች ባደረጉልኝ ድጋፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስመር ከዘራሁት ሰሊጥ በሄክታር ከሰባት ኩንታል በላይ ምርት አግኝቻለሁ" ያሉት ደግሞ  የአደባይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰዓደ መሀመድ ናቸው።

ያገኙት ምርት ከተለምዶ ሲያመርቱት ከነበረው እስከ ሁለት ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

የወረዳው የአዝርእት ልማት ኃላፊ አቶ ገብረሕይወት ኃይሉ በአርሶ አደሮች ደረጃ በአንድ ሄክታር በአማካይ እየተገኘ ያለውን ስድስት ኩንታል የሰሊጥ ምርት ለማሳደግ ዘመናዊ አመራረት ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል ።

የሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል የሰሊጥ ተመራማሪ አቶ ይርጋ በላይ በበኩላቸው ማዕከሉ የሰሊጥ ምርታማነትን ለማሻሻል ምርጥ ዝርያዎችን በማውጣት በአርሶ አደሩ ማሳ እያላመደ መሆኑን ገልጸዋል ።

በመኽር ወቅቱ  ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የተሻሻለ የሰሊጥ ዝርያን በመስመር በመዝራት በተካሄደ የሙከራ ልማት የተሻለ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል ።

እንደተመራማሪው ገለጻ ማዕከሉ የጀመረውን የሰሊጥ ምርታማነት የማሻሻል ስራ በቀጣዩ ምርት ዘመን ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች ያስፋፋል ።

በወረዳው በ2011/12 ምርት ዘመን የመኽር ወቅት ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 388ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 200 ሺህ ሄክታሩ በሰሊጥ የተሸፈ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም