በጋሞ ጎፋ ዞን ለአራተኛ ክፍል ዞናዊ ፈተና ዝግጅት ተጠናቋል

1388

አርባምንጭ 12/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን ሰኔ 14 እና 15 ቀን 2010 ለሚሰጠው ዞናዊ የአራተኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት መጠናቁን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ማሔ ቦዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎች የዘንድሮውን ዞናዊ ጥቅል ፈተና ለመውሰድ ተመዝገበዋል።

የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከመራዘም ጋር ተያይዞ የአራተኛ ከፍል ፈተናም ተራዝሟል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለፈተና ቁሳቁሶች ጥንቃቄ ተደራጅቶ ወደ ፈተና ጣቢያዎች መሠራጨታቸውን ገልጸዋል።

የስራ ስምሪት የተሰጣቸው የፈተና አስተባባሪዎችና ጸጥታ አስከባሪዎችም ወደ ተመደቡበት ጣቢያ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የሚሰጠው ዞናዊ የአራተኛ ክፍል ፈተና በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ብቸኛው ሲሆን በአምስት ትምህርት ዓይነቶች የሚሰጥ ነው።

የዘንድሮ ዞናዊ ጥቅል ፈተና ከ160 በላይ የፈተና አስተባባሪዎች በ72 ክላስተሮች እንደሚሰጥ ከመምሪያው የተገኙ መረጃ ያመለክታል።