የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

41
ጋምቤላ ሰኔ 12/2010 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ባለፈ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን የማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አምባሳደር ገነት ዘውዴ ገለጹ። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላለፉት ሁለት ቀናት በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል። በክብር እንግድነት የተገኙት አምባሳደር ገነት ዘውዴ እንዳሉት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን ችግሮች በሚፈቱ የምርምር ስራዎች ላይ ጭምር ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። ''በተለይም የተቋማቱ መምህራን በእውቀትና በስነ-ምግባር የተገነባ ዜጋ ከመፍጠር ባለፈ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ለማህበረሰቡ ለውጥና ለሀገሪቱ እድገት መስራት ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል። በምርምር ጉባኤው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የቀረቡት ጥናታዊ ጹሁፎች በማህበረሰቡና በሀገሪቱ ችግሮች ዙሪያ ያተኮሩ መሆናቸው ተስፋ ሰጪም እንደሆነ ጠቁመው የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተቋማቱ በምርምር የተገኙ ውጤቶች ወደ ህዝቡና መንግስት ተቋማት ደርሰው የታለመውን ችግር ይፈቱ ዘንድም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ የአካባቢን ማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት እየሰራ ነው። በዩኒቨርሲቲው የተካሄደው የምርምር ጉባኤም ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  ልምዶችንና ተሞክሮዎች በመውሰድ የተሻሉ የምርምር ስራዎች ለማከናወን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር መርከብ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በርካታ ችግር ፍቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወኑ ቢሆንም የምርምር ውጤቶቹ ወደ ህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ እየወረዱ አይደለም ። ስለሆነም የምርምር ውጤቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግብዓት ብቻ ከመሆን አልፈው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት የአሰራር ስልት መቀየስ እንዳለበት ተናግረዋል። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክተር አቶ በሱፍቃድ እንደግ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የዚህን ዓመት ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ65 በላይ የምርምር ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የምርምር ውጤቶቹ ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመው  በቀጣይ አቅም በፈቀዱ ሁኔታ ወደ ህብረተሰቡ ለማወረድ ይሰራል ብለዋል። ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምርምር ጉባኤ ከ17 ዩኒቨርሲቲዎች በግብርና፣ በግጭትና በሰላም ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎችም የማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ የምርምር ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም