የመጀመሪያው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ከሰኞ ጀምሮ ይካሄዳል

96
ጥቅምት 21/2012 "ትኩረት ለሳይበር ደህንነት" በሚል መሪ ሀሳብ የመጀመሪያው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ከሰኞ ጀምሮ ይካሄዳል። ይሄው ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደው የብሔራዊ ሳይበር ደህንነት ሳምንት ክንውኖች በአፍሪካ ኢኮኖሚ አዳራሽና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መሆኑ ተጠቁሟል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ(ኢንሳ) ሳምንቱን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ሳይበር የኮምፒዩተሮችን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ምናባዊ እውነታን(ቨርቹዋል ሪያሊቲን) ባህሪያትና መገለጫን አካቶ የያዘ ማለት ነው። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በዓለም ላይ ከሚደርሱ የሳይበር ጥቃት 90 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ከሰዎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ችግር የሚመነጭ መሆኑን አመልክተዋል። የንቃተ ህሊና ችግሩ የሚመነጨው ሰዎች በሳይበር ዙሪያ ባላቸው የግንዛቤ ክፍተት ምክንያት እንደሆነም ተናግረዋል። የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ማሳደግ የሳይበር ጥቃትን በመከላከል ስራ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል። ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ማዘጋጀት ያስፈለገበትም ምክንያት የህብረተሰሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማሳደግና አቅምን ለማጠናከር እንደሆነ ነው ኢንጂነር ወርቁ የገለጹት። የተለያዩ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ከማድረግ ባሻገር የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚችሉበት ሁኔታ ላይ መድረስ እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አመልክተዋል። አገራዊ የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች እንደሚታዩ የጠቆሙት ኢንጅነር ወርቁ፤ በኤጀንሲውና በሌሎች ተቋማት የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ገለጻ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት መምጣቱንና ቴክኖሎጂው ባደገ ቁጥር ለሳይበር ጥቃት መጋለጥ እንደሚጨምር አመልክተው፤ ለዚህም ጥቃትን የመከላከል አቅም የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የሳይበር ጥቃትን መከላከል የኤጀንሲው ተግባር ቢሆንም ተቋማትን ለጥቃት እንዳይጋለጡ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። በመጀመሪያው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት 1 ሺ 100 የሳይበር ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ይታደሙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። በ2011 ዓ.ም 791 የሳይበር ጥቃቶች ደርሰው ለ80 በመቶው የመከላከል ምላሽ መሰጠቱን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 113 የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመው፤ ለ83 ነጥብ 7 በመቶው የመከላከል ምላሽ ተሰጥቷል። ኤጀንሲው የኢትዮጵያን ኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ ተልዕኮው አድርጎ እየሰራ ይገኛል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም