የአርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

446
ሽረ እንዳስላሰ (ኢዜአ) ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እያደረጉት ያለው ጥረት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታውና የአሊያንስ ፎር ግሪን ሪቮለዩሽን ኢን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር በተገኙበት የመስክ ምልከታ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ታህታይ ቆራሮ ወረዳ ተካሂዷል። በእዚህም “ቁንጨ” እና “ ኮራ” የተበሉ ምርጥ የጤፍ ዘሮችን ተጠቅመው ያለሙ የታህታይ ቆራሮ አርሶ አደሮች ማሳቸው ተጎብኝቷል፡፡ የግብርና ሚንስትር ዲኤታው ዶክተር እያሱ አብርሃ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ከእዚህ ቀደም ያልነበረው ጤፍን በመስመር የመዝራት ልምድ በአሁኑ ወቅት እያደገ መጥቷል፡፡ ይህም ጤፍን በብዛትና በጥራት ለማምረት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ "አርሶ አደሮች የምርት ግብአቶችን በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ በኩታ ገጠም በማልማት ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እያደረጉት ያለው ጥረትም አበራታች ነው" ብለዋል። “ግብርናውን ለማዘመን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል” ያሉት ሚንስትር ዴኤታው በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች እየታየ ያለው አበራታች ለውጥ ወደሁሉም አርሶ አደሮች ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ለውጡ ወደሁሉም አርሶ አደሮች እንዲዳረስ በማድረግ በኩል "አሊያንስ ፎር ግሪን ሪቮለዩሽን ኢን አፍሪካ" የተባለ ድርጅት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ሚንስትር ዲኤታው ተናግረዋል። በመስክ ግብኝቱ ላይ የተሳተፉት የአሊያንስ ፎር ግሪን ሪቮለዩሽን ኢን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አግነስ ካሊባታ በበኩላቸው አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ስልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ የገቡ አርሶ አደሮች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ መልካም ጅምር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ "ሴት አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ መጎልበት አለበት" ሲሉም ዶክተር አግነስ ተናግረዋል። በግብርና ዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ የግብርና ሚንስቴር እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ድርጅታቸው የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ዳይሬክተሯ ያረጋገጡት። ማሳቸው ከተጎበኘላቸው የታህታይ ቆራሮ ወረዳ አርሶ አደረች መካከል አርሶ አደር በላይ ቢሆን “ቁንጨ” የተባለ ምርጥ የጤፍ ዘር ተጠቅመው ያለሙት ማሳቸው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በምርጥ ዘር እየለማ ካለው አንድ ሄክታር ማሳቸው ከሃያ ኩንታል በላይ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡ “ኮራ” የተባለ ምርጥ የጤፍ ዘርን በመስመር ዘርተው እያለሙ ያሉት ሴት አርሶ አደር ገብርኤላ ፀጋይ በበኩላቸው ሰብሉ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ በመድረሱ ከእስከዛሬው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት በኩታ ገጠም ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳቸው ከ18 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁም አመልክተዋል። “ምርጥ ዘር ተጠቅሜ በመስመርና በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ያለማሁት የጤፍ ማሳ በጥሩ የእደገት ደረጃ ነው ያለው”ያሉት ሌላው የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደሳለኝ አብርሃ ናቸው። "ከአንድ ሄክታር ማሳዬ ከ20 ኩንታል በላይ ምርት እጠብቃለሁ" ብለዋል። አርሶ አደሮቹ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተከትለው ያመረቱትን ምርጥ ዘር በጥንቃቄ በመሰብሰብና ሌሎች አርሶ አደረች በማቅረብ በአካባቢያቸው ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እነዚህ አርሶ አደሮች እንዳሉት ቀደም ሲል የአካባቢው የጤፍ ዘር በመጠቀም ሲያለሙ ከሄክታር ከአስር ኩንታል በላይ አግኝተው አያውቁም።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም