ፍሬወይኒ መብራህቱ ከዓለም 10 ምርጥ የሲ ኤን ኤን የ2019 "ጀግና" አንዷ ሆኑ

58
ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓም (ኢዜአ)  በየዓመቱ በሚከናወነው የሲ ኤን ኤን ቴሌቭዥን ምርጫ የ2019 ጀግና ተብለው ከተለዩት አስር ግለሰቦች መካከል አንዷ ሆነው መመረጣቸውን የማሪያም ሳባ የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ፋብሪካ መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ ገለጹ። የቴሌቭዥን ጣቢያውም ከዓለም አስር ምርጥ ስራ ፈጣሪ ጀግኖች አንዷ በመሆናቸው የ10 ሺህ ዶላር ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ይሄንን አስመልክቶ ወይዘሮዋ ለኢዜአ እንደገለጹት ለዚህ ካበቃቸው ስራዎች ዋነኛው ማሪያም ሳባ በተባለው የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ፋብሪካቸው በርካታ የአካባቢውን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ይህ ጥረታቸውም ለዚህ ስላበቃቸው መደሰታቸውን ገልጸው የቴሌቭዠን ጣቢያው በመጀመሪያ ዙር ካቀረባቸው 25 ግለሰቦች መካካል እሳቸው በምርጥ አስሩ ውስጥ መካተታቸውን አስረድዋል። በቀጣይም ከወር በኋላ የ100 ሺህ ዶላር አሸናፊ በሚያደረገው ምርጫ ላይም ህብረተሰቡ በድረ-ገጹ /www.cnn.comspecials/cnn¬-heros በመግባት ድምጽ በመስጠት እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ለብዙ ዓመታት በአሜሪካ ከኖሩ በኋላ ወደ መቀሌ ከተማ መጥተው ከ50 ሚልዮን ብር በሚልቅ ወጪ ከስድስት ዓመታት በፊት የከፈቱት ፋብሪካ ዛሬ ላይ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ጥቅል በላይ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ እያመረተ እንደሚያከፋፍል ገልጸዋል። በዚህም በተለይ የገጠር አከባቢ ሴት ተማሪዎች ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መጠቀም በመጀመራቸው በትምህርት ገበታቸው መስተጓጎል እንዳያጋጥማቸው እያገዘ መሆኑንም ጠቁመዋል። ፋብሪካው በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለማስፋፋትና ሁሉም የሃገራችን ሴቶች አቅማቸው በሚፈቅድ መንገድ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ለ42 የአካባቢው ሴቶች የስራ እድል የፈጠረው ይህ ፋብሪካ ምርቶቹ የተሻሻሉና የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ከውጭ ከሚገቡት ተመሳሳይ ምርቶች በ80% የዋጋ ቅናሽ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በእጩነት ተለይተው የ2019 ጀግና በሚል በቴሌቭዥን ጣቢያው ከተመረጡት 10 ግለሰቦች መካከል  እሳቸውን ጨምሮ አራቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም