ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ

74
ሶዶ ሰኔ 12/10/2010 ለወላይታ ሶዶ ከተማ ዘላቂ  ሰላም መረጋገጥ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰላም እንዲሰፍን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። የወላይታ ዞን ደኢህዴን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የከተማ ዘርፍ ፖለቲካ ኃላፊ አቶ ደጉ ካሳ "በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የደረሰው አደጋ አስደንጋጭና ሃዘን ጥሎ ያለፈ ክስተት ነው" ብለዋል። የደቡብ ክልል ካለው ባህላዊና ነባር ዕሴት ጋር በሚጻረር መልኩ ግጭቱን ወደሌላ አቅጣጫ ለማዞር የተሞከረው ሂደት ያስከተለው ግጭትና ውድመት ተቀባይነት የለሌው ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል። ''የአገሪቱን ልማት በማስቀጠል የክልሉን ተጠቃሚነት በሚፈለገው መልኩ ለማረጋገጥ ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው'' ያሉት ኃላፊው ''ከተማውን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የሶዶ ከተማና የአካባቢው ማህበረሰብ በትኩረት ሊሳተፍ ይገባል'' ነው ያሉት። መንግስት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአደጋ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከሚመለከታቸው አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል። በክልሉ ባልተለመደ ሁኔታ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሄ እንዲሰጠውና ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ያለስጋት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። በሶዶ ከተማ የቆንቶ መንደር ነዋሪ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ተክሌ በከተማዋ በድንገት የተከሰተው የጸጥታ ችግር በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት "ከፍተኛ ሃዘን ጥሎብን አልፏል" ሲሉ ገልጸዋል። ችግሩን ተጠቅመው የህዝብና የመንግስትን ንብረት ለጉዳት የዳረጉ አካላትን ዕኩይ ተልዕኮ በመረዳት በየመንደራቸው ለሰላም ዘብ ለመቆምና የሚታወቁበትን ሰላማዊ አኗኗር ለመመለስ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩት የሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ያዕቆብ አልታዬ በቅርብ ጊዜ እየተፈጠረ የመጣው የጸጥታ ችግር በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው ይላሉ። በተለይም "ሳይታሰብ በተፈጠረው ችግር የሰዎች ህይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ ወደኋላ የሚጎትተን በመሆኑ ልንነቃ ይገባል" ብለዋል። በሶዶ ከተማ የተስተዋለውን የጸጥታ ችግር ወደነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመቀየርና ልማቱን ለማስቀጠል ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል። በሶዶ ከተማ የዋዱ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ወንድማገኝ ማቴዎስ "ዓለም ወደደረሰበት ለመድረስ መስራትና መሮጥ ሲገባን የጸጥታ ችግር በመፍጠር ውድ የሆነው የሰውን ህይወትና ንብረት መውደሙ በወጣቱ ዘንድ መወገዝ አለበት" ብሏል። ልማትና የስራ ዕድል እየተፈለገ፤ ህዝብ ለህዝብ የተጋጨ በማስመሰል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በተለያዩ አካላት የተበጀ ሴራ መሆኑን ወጣቱ በመረዳት ሰላሙን ለመመለስ መስራት ይኖርበታል ነው ያለው። አሁኑ ወቅት በሶዶ ከተማ በህዝቡ ተሳትፎ አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መሆኑ አስደሳች መሆኑን ገልጾ ይህን በማጠናከር ወደቀድሞው ሰላምና መረጋጋት ለመምጣት በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጸው። መንግስት በተለይም የወጣቱን ጥያቄ መመለስ አለበት ያለው ወጣት ወንድማገኝ ግጭት የፈጠሩ ግለሰቦች ለህግ መቅረብ አለባቸው ብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም