በትግራይ የግል ባለሃብቶች የመስኖ ልማት ስራ ግብርናን ለማዘመን የተጀመረውን ጥረት ያፋጥናል - ዶክተር ሙላቱ

57
መቀሌ ሰኔ 12/2010 በትግራይ ክልል የግል ባለሃብቶች የሚያካሂዱት የመስኖ ልማት ስራ ግብርናን ለማዘመን የተጀመረውን ጥረት እንደሚያፋጥን  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ራያ አዘቦ ወረዳ በግል በለሃብቶች እየተካሄዱ ያሉት የልማት ስራዎች  ትላንት ጎብኝተዋል። ፕሬዚዳንት ሙላቱ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት ባለሃብቶቹ ግብርናን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ባለሀብቶቹ  በውጭ  ተፈላጊ በሆኑ ምርቶች ማተኮራቸው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ ለዘመናት  በዘልማድ  የቆየውን የግብርና ስራ ለማዘመን እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ''የባለሃብቶቹ ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት ጥረት ይደረጋል'' ብለዋል፡፡ የአካባቢው አርሶአደሮች ባላቸው አቅም ከባለሃብቶቹ ጋር ተቀናጅተው እንዲያመርቱ የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ለባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡ ግብርናን ከኢንዱስተሪ በማስተሳሰሩ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በምርምር የወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎችና ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፌዴራል መንግስት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ  የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እያሱ አብርሃ ናቸው። ከቀጣዩ አመት ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በመደገፍ በሰፋፊ የመስኖ  እርሻዎች እንዲለሙ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር ላይም ትኩረት ለመስጠት መንግስት ዋነኛ አጀንዳው መሆኑን ገልፀዋል። በአንድ የውጭ ባለሀብት ከሶስት ዓመታት በፊት በ32 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በ1ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ በመካሄድ ላይ ያለው የመስኖ ልማት ፕሬዝደንቱ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከጎበኙት መካከል አንዱ ነው። ‘’ ቫልቨርድ ፉድስ ’’  በሚል ስያሜ በአንድ የስፔን ባለህብት ስድስት የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች እሴት በመጨመር ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ተገልጿል፡፡ በራያ ዓዘቦ ወረዳ የቫልቨርድ ፉድስ ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ንጉሰ እንገለፀት  ኘሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የውጭ ገበያን ትኩረት አርድጎ በመስራት ላይ መሆኑን አስረድቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም