ጋሞዎች የሰላም ተምሳሌቶች

157
     ሳሙኤል አያነው/ አርባ ምንጭ ኢዜአ/ “ኢትዮጵያዊያን ፍቅር የለም ብለንተስፋ ለመቁረጥ በተቃረብንበት ወቅት ፍቅርማ አለ የምን ተስፋ መቁረጥ? የሚለን የጋሞ ህዝብ ነው። የ40ዎቹ ምንጮች ምድር፣ በፍራፍሬ የታደለው ስፍራ፣ በዓሣ ሀብት የሚታወቀው ጋሞ ተሸንፈው የሚያስታርቁ ለዓለም አርአያ ለእኛ ደግሞ ኩራት የሆኑ ሽማግሌዎች ባለቤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም አኩሪ ባህል፣ታሪክና ኃይማኖት እንዳለ ላስተማሩን ለጋሞ ዕንቁዎች ብቻ ሳይሆን ለፈጠራቸውም ምስጋና ይግባው ፡፡ የገነፈለን ማብረድ እንደሚችሉ በተግባር አስተምረውናልና፡፡ ለውጥና ሰላም ናፋቂዎች የሽምግልናን ወግ ከጋሞ ህዝብና ሽማግሌዎች መማር ይችላሉ ። እንደጋሞ ሽማግሌዎች ዝቅ ብለን በማስታረቅ ለአገር ሰላምና ፍቅር ከደከምን ፣አንድነትን ከሰበክንና ካስተማርን የምንመኘውን ሰላም ማረጋገጥ የማንችልበት ምክንያት አይኖርም ። የጋሞዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ልምድ ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ዛሬን ሊደርስ የቻለው አባቶች የተረከቡትን የግጭት መፍቻ አደራ ቁልፍ በሚገባ በመጠበቃቸው ነው፡፡ ይህን አኩሪ ባህል ማስቀጠሉ የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ሲሆን በአግባቡ ጠብቆና ተንከባክቦ ዘመን ማሻገር ከቻለ እንደአባቶቹ ተመስጋኝ ካላደረገው ግን የታሪክተወቃሽ መሆኑአይቀርም። ከጋሞ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሰዲ ቃስሜ እንደሚሉት ህግ እስከዛሬ የሰው ልጆችን ህሊና ሙሉ በሙሉ ሊገዛ አልቻለም። የጋሞ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ግን ህሊናን የሚዳኝና የሚገዛ ነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ በሁለት ወገኖች መካከል ቂም አልባ እርቅ ይፈጸማል፡፡ ይህ ደግሞ በዘላቂነት አብሮ ለመኖር ዋስትና ያለው በመሆኑ ጋሞዎች እርስ በርስ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተፈቃቅረው ለዘመናት እንዲኖሩ አስችሎአቸዋል፡፡ ሌላውና ትልቁ ነገር ደግሞ የአባቶችን ወይም የእናቶችን ምክር ተላልፎ ግጭት ለመፍጠር መቃጣት ፈጽሞ እንደሚያስቀጥፍ ጋሞዎች የሚያምኑት እሴት ነው ፡፡ አሻፈረኝ የሚል ቢኖር ከማህረሰቡ እንዲገለል የሚያደርገው አሰራርም ሌላኛው የማህበረሰቡ ጠቃሚ እሴት ነዉ፡፡ በጋሞዎች 42 ደሬዎች፣ህዝቦች ወይም አከባቢዎች የሚገኙ ሲሆን የየራሳቸዉ ተወካይ አምባሳደሮች አሉዋቸው፡፡ የእርቅ ስነ-ስርዓታቸውን በአጭሩ ስንመለከት በሁለት ወገኖች መካከል ፀብ ወይም ግጭት ቢፈጠር የባህል አባቶች “ዱቡሻ “በተሰኘው የእርቅ አደባባይ ላይ ተሰይመው የሁለቱ ወገኖችን ጉዳይ ካጣሩ በኋላ ጥፋተኛው በጥፋቱ ተጸጽቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረጋል እንጂ ካሣ አይከፈልም ፡፡ ካሣ የአብሮነት እሴቶቻቸውን የሚጎዳ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉና፡፡ አቶ ሰዲቃ ”ጋሞዎች የኢትዮጵያ ምድር ለኢትዮጵያዊያን እንግዳ ልትሆን አይገባትም” ብለው ያምናሉ ። በተለይም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በየአከባቢው የሚከሰቱትን የእርስ በርስ ግጭቶች ማህበራዊ ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን በማጣቀስ ። በመሆኑም ብሔራዊ ማንነታችን ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ለይተን አናይም ባይናቸው። የራሳችን ብሔራዊ ማንነት እንዲነካ እንደማንፈልግ ሁሉ የሌሎችንም ማንነት መንካት ከቶ አይቻልም ይላሉ፡፡ ይህን ማረጋገጥ የሚቻለዉ ደግሞ ጋሞዎች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብረው ከመኖርውጭ በማንነቱ ከጋሞ ምድር የተገለለና የተሰደደ አለመኖሩን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ አኩሪ ልምድ ለአገራችን ሰላምና ልማት እንዲሁም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን ቢወጡ መልካም ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ ሌላኛው የጋሞ አባት አቶ አዳሙ ኪሮ ደግሞ የእርስ በርስግጭቶች የሰው ልጆች በዚህ ምድር እስካለድረስ መኖራቸው እንደማይቀር ያምናሉ፡፡ ጋሞዎች ግጭቶችን ጉዳት ሳያደርሱ የሚፈቱበት መንገድግን ለሌላው ማህበረሰብ ተምሳሌት የሚሆን ነው ባይናቸው ፡፡ ከተራ ዛቻ ጀምሮ እስከ ህይወት ማጥፋት የደረሱ ጉዳዮችን በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቱ ይታያሉ ። 42ቱ ደሬዎች የየራሳቸዉ “ዱቡሻዎች” ወይም የፍትህ አደባባይ ያሏቸው በመሆኑ በደሬዎች /ህዝቦች/ ፀብ ቢቀሰቀስ የህዝቡ ባህላዊ አምባሳደሮች እርጥብ ሳር ይዘውና ተንበርክከው ለሰላም ሲዘጋጁ ሁሉም ባለበት ይቆማል፡፡ ይህ ልምድ የሰው ህይወትን ከማዳን ባለፈ ገንዘብና ጊዜን በመቆጠብ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው ፡፡ በጋሞዎች ዘንድ በእርቅ ጉዳዩ ካለቀ በኋላ ቂምና በቀል የሚባል ነገር ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ይህን ህዝብ ለማስተዳደር የታደሉት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ደግሞ በዞኑ ከ1ነጥብ7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚኖሩ ጠቅሰው ጋሞ ዘይሴና የጊዲቾ ብሔረሰቦች ነባር ቢሆኑም ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ተከባብረውና ተቻችለው ይኖሩበታል ። ዞናችን የሰላም አምባሳደር ነው የሚሉት አስተዳዳሪው ቁጣ አብራጁ የጋሞ ባህል የመደመር ፍልስፍናን አስቀድሞ የተገበረ በመሆኑ አርባ ምንጭ ከተማ የቱሪዝም ኮንፈረንስ መናኸሪያ ሆናለች፡፡ በሰበታና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከጋሞዎች ጋር ተያይዞ ይነሳ የነበረው ችግርም በባህሉ መሰረት በይቅርታ መሻገር ተችሏል ። ጥፋት መስራት ቀላል ነው የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት እየተቻለ የእርስ በርስ ግጭት መፈጠር የለበትም ። የሰው ልጅ ክቡር በመሆኑ በተሟላ ግብረ-ገብነት ሊታገዝ እንደሚገባው አስረድተዋል ። ለዚህም ነው የጋሞ ማህበረሰብ በቀልን የማያውቅና ባህሉንና ወጉን አጥብቆ የሚያከብር ህዝብ ሆኖ የዘለቀው፡፡ የጋሞ አገርበቀል የግጭት አፈታት ዘዴ ዘመናዊ የአስተዳደር ስርአትን በመደገፍ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘም አብራርተዋል። ልምዱን ለአገራዊ አንደምታ ለማዋል በሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የዞኑ አስተዳደርና ህዝቡ ፍቃደኛና ተባባሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሰላም እንድሰፍን የሰው ልጆች እርስ በርስ በአብሮነት፣ በመቻቻል፣ በመተሳሰብና በፍቅር መኖር አለበት፡፡ ያለሰላም ወጥቶ መግባት ፣ መማር ማስተማር፣ መነገድም ሆነ ማረስ በአጠቃላይ የመኖር ህልውናም አይታሰብም ፡፡ ለዚህ ነው ጥላቻን አስወግደን የፍቅር ድልድይ እንገንባ ፣ እንደመር የሚል ጥሪ ተደጋግሞ የሚተላለፈው ። የጋሞዎች የሰላም ተምሳሌትነት በአገር ደረጃ እውቅና ከማግኘቱም በላይ የዓመቱ የበጎ ሰው ልዩ ሽልማት ማግኘቱ በበጎ ስራ የተገኘ በጎ ውጤት መሆኑን ያሳያል ። መልካምነት ለራስ ነው ። በተለይ መደመር ለጋሞዎች ትናንት የነበረ፣ ዛሬ ያለና ነገም የሚኖር ባህል በመሆኑ ልንኮራበት ይገባል ። ጋሞዎች የሚመክሩ ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ የሚሰሙ ወጣቶችም ያሉዋቸው በመሆኑ በተለይ ወጣቱ አገር ያኮራውን የአባቶቹን የሰላም ተምሳሌትነት ለመጪው ትውልድ የማቆየት ኃላፊነት እንዳላቸው ጠንቅቀው የተገነዘቡ በመሆናቸው ሁላችንም ኮራንባቸው ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም