በ10 ዓመታት ውስጥ ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

67
ኢዜአ ጥቅምት 19/2012 ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የ300 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ። የስራ ዕድሉን ለመፍጠር ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የመጀመሪያ ዙር 300 ሚሊዮን ዶላር በጀት መድቧል። የስራ ፈጠራ ኮሚሽን በተያዘው ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች አዳዲስ ስራዎችን ለመፍጠር አቅዷል። ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት የምትመራበትን የስራ ዕድል ፈጠራ እና 20 ሚሊዮን ወጣቶችን ወደ ስራ የሚያስገባ ዕቅድ በነገው ዕለት ይፋ ያደርጋል። 'ወጣቷ አፍሪካ ትሰራለች' የተባለውን ፕሮጀት የስራ ፈጠራ ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ፣ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሪታ ሮይ እና የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ኮንዴ ይፋ አድርገዋል። ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ከስራ ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በአምራች ኢንዱስትሪና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጿል። የስራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አጋርነት ተግባራዊ የሚደረገው የ10 ዓመት ዕቅድ ከመንግስት ዕቅድ ጋር ተያያዥነት አለው። የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሪታ ሮይ በበኩላቸው ''ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት በአገሪቱ በርካታ ዕድሎችና ስራ ፈላጊ ወጣቶች ስላሉ ነው'' ብለዋል። ፕሮጀክቱ ለወጣቶች የገንዘብ አቅርቦት፣ የቢዝነስና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠናዎች እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ኃላፊ አቶ አለማየሁ ኮንዴ እንዳሉት፤ ፋውንዴሽኑ በአፍሪካ ለ30 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ከያዘው ዕቅድ ውስጥ 10 ሚሊዮኑ በኢትዮጵያ እንዲሆን ተወስኗል። በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች ስራ ለማስያዝ የሚያስችሉ ዘርፎች የትኞቹ እንደሆኑ መለየታቸውን ገልጸዋል። ፋውንዴሽኑ ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ ባሉ 34 አገሮች ውስጥ ሰርቷል። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በታየው የግሉን ዘርፍ ልማት ቁጥጥርና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ስራ ፋውንዴሽኑ በስራ ዕድል ፈጠራ አገሪቱን ቅድሚያ እንዲሰጣት አድርጓታል። ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ እንዲጠናከር በመንግስት ዕቅድ መያዙ ይታቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም