ለሶስት የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሊሰጥ ነው

89
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 19 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ለሶስት የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ መውጣቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ለኢዜአ እንደተናገሩት በአዲሰ አበባ ለሶስት ኤፍ ኤም ሞገዶች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ወጥቷል። በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡ ተጫራቾችን በመለየት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ባለስልጣኑ አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሞት ጨረታውን ካልሰረዘ በስተቀር ሂደቱን በማጠናቀቅ ፈቃድ እንደሚሰጥ  አስረድተዋል። እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር መጨመር የህብረተሰቡን መረጃ የማግኘት አማራጭ ያሰፋዋል። በሌላ በኩል በተያዘው ዓመት ለማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ እንደማይሰጥ ገልጸዋል። በመሆኑም ባለስልጣኑ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎችን የማጠናከር ተግባር ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል። የተቋቋሙ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በአቅም ማነስና ሌሎች ችግሮች እየተንገዳገዱ ባሉበት ሁኔታ አዲስ መክፈት አስፈላጊ አለመሆኑን ነው የገለጹት። በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ፣ በአስተዳደር ክህሎትና በይዘት በማብቃት በሚሰራጩበት አካባቢ ለሰላም መስፈን ያላቸውን ተግባር እንዲወጡ ይሰራል ብለዋል። የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር እንዲጨምር ከማድረግ ጎን ለጎን ሙያን መሰረት በማድረግ የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩም ለማገዝ ባለስልጣኑ አቅም የማጎልበት ተግባር እንደሚያከናውንም ተናግረዋል። ለዚህም ከኳታር መንግስት ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ማዕከል ለመገንባት መታቀዱን ነው አቶ ወንድወሰን ያስታወቁት። ማዕከሉን ለመገንባት የኳታር መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸው ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል። ሙያን መሰረት ያደረገ የስራ ላይ ስልጠና ይሰጥበታል የተባለው ይህ ማዕከል የብሮድካስት፣ የህትመት፣ የዲጂታልና ሌሎች ለስልጠና የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በውስጡ ይይዛል ተብሏል። ማሰልጠኛውን የምስራቅ አፍሪካ የስልጠና ማዕከል ለማድረግም ታልሟል። በኢትዮጵያ ከ70 በላይ የማህበረሰብና የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች እንደሚገኙ የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም