የከተሞች የመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ አሰራር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የከተሞች የመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ አሰራር ይፋ ሆነ
124
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2010 የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተሞች የመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረገ። ሚኒስቴሩ ''ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አቅርቦት በከተሞችና በአገልግሎት ስታንዳርዶች አስፈላጊነት ላይ'' በሚል ዛሬ ውይይት አድርጓል። በዚህ ወቅትም በመሬት አቅርቦት፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ፣ በሕዝብና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ በቄራና በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች፤ እንዲሁም በዘላቂ ማረፊያ ስታንዳርዶች ላይ አዲስ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ይፋ አድርጓል። አሰራሩ በአገሪቱ 142 ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን በሚኒስቴሩ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥዑማይ በርሄ ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በከሚሴ፣ በውቅሮና አዲግራት ከተሞች በሙከራ ደረጃ ሲተገበር መቆየቱን ገልጸው፤ አበረታች ውጤት መታየቱን ጠቁመዋል። በመሆኑም ተሞክሮውን በማስፋት አሰራሩ ከዛሬ ጀምሮ በሁሉም ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል። ተግባራዊ የሚደረገውም የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራር የሚታይባቸውና ሕዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው ዘርፎች ላይ ነው ብለዋል። በመሆኑም የሕብረተሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አስፈፃሚ አካላት አሰራሮቹን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ቢራሳ በበኩላቸው የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ አኳያ የከተሞቹ የአመራር አካላት ለተግባራዊነቱ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። መገናኛ ብዙሃንም ለህብረተሰቡ የአሰራር መስፈርቶቹን በማሳወቅና በማስገንዘብ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ህብረተሰቡም በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት መብቶቹን በመገንዘብ አድሎአዊ አሰራርና መጉላላት የሚፈጥር ባለሙያና አመራርን ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል።