ወልቂጤ በተሻለ ሰላምና መረጋጋት ላይ ይገኛል

119
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2010 ባለፈው ሳምንት ግጭት ውስጥ የነበረው የወልቂጤ ከተማ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት በማግኘቱ ሕብረተሰቡ የተለመደ የዕለት ተግባሩን መከወን እየጀመረ ነው። በከተማዋ በሚኖሩ የጉራጌና ቀቤና ብሔረሰብ መካከል ተከስቶ  በነበረው ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የጉራጌ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ወልደማርያም በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ተናግረዋል። የመንግስት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ባደረጉት የማረጋጋት ተግባርና መንግስት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባስተላለፉት የሰላም መልዕክት አሁን በከተማዋ መረጋጋት እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ኃላፊው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በነገው ዕለት ከአንድ ሺህ በላይ ከሚሆኑ የከተማውና የዞኑ ሕብረተሰብ ተወካዮች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ከሌሎች የማህበረሰብ አካላት ጋር ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ዙሪያ ይወያያሉ። ነዋሪው የጠቅላይ ሚንስትሩን መምጣት እየተጠባበቀ መሆኑም ተወስቷል። አቶ ፋንታሁን እንዳሉት በወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የሚነሱ የማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ የተጠቃሚነት ጥያቄዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የጤና፣ የመጠጥ ውሃ፣ የኤሌትሪክ፣ የስራ አጥነት፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ይጠቀሳሉ፤ ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ይጠበቃል ነው ያሉት። የከተማውን ልማት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የሚታሰበውን መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) ስራ ላይ ለማዋል ከሕብረተሰቡ ጋር ግልጽ ውይይት ይደረጋል፤ በዚህም በተለይ በከተማው አዋሳኝ የሚገኙትን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ርዕሰ መዲና ወልቂጤ ከ200 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም