በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚያሻሽል አዲስ መመሪያ ይፋ ሆነ

96

አዲስ አበባ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ጤና ሚኒስቴር በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚያግዝ መመሪያ ይፋ አደረገ።

መመሪያው ለአምስት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ህክምና በሚሰጥበት ወቅት ታካሚዎች ተጨማሪ መበከል (ኢንፌክሽን) ችግር እንዳይገጥማቸውና የአገልግሎቱን ጥራት ከፍ ያደርጋል ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በጥናት እንዳስቀመጠው 10 ገዳይ ብሎ ካስቀመጣቸው በሽታዎች መካከል ደህንነቱ ባልተጠበቀ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚከሰተው አንዱ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የጠቅላላ ሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሴማን መመሪያውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በየሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ንጽህና የጎደለው ነው።

በጤና ተቋማት ያለው አካባቢ ንጽህናው ያልተጠበቀ በመሆኑ ህክምና ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች እንዲቀንሱ እያደረገ ነው ይላሉ።

ታካሚዎች ለተጨማሪ ባክቴሪያዎች የመበከል ችግር ሳያጋጥማቸው ውጤታማና ንጽህናውን ጠብቆ አገልግሎቱን አግኝተው እንዲያገግሙ የሚያስችል አሰራርን መከተል በማስፈለጉ አዲሱ መመሪያ መዘጋጀቱን ነው የሚገልጹት።

በጤና አሰጣጡ ሂደት ከቅድመ ህክምና ጀምሮ ተገልጋዩች እስኪያገግሙ ድረስ የሚያጋጥም የማመርቀዝ ሁኔታን መቀነስና መከላከል እንዲቻል፤ እንዲሁም ህክምና በመስጠት በሽተኛው ደህንነቱ የተጠበቀና ተጨማሪ ችግር እንዳይገጥመው ማድረግ ነው ብለዋል።

''መመሪያው መበከል(ኢንፌክሽንን) መቆጣጠርና መከላከል ግንዛቤን የሚያሳድግ፣ በኢትየጵያ ጤና ተቋም ውስጥ ያሉ የመበከል ሁኔታዎች ምን ይመስላሉና ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትን የሚያሳይ ነው'' ሲሉም አብራርተዋል።

በተለይም የእጅ መታጠብና በቅድመ ቀዶ ህክምና ወቅት መከተል የሚገባቸው ሂደቶችና ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ ባለሙያውና ተገልጋዩ ማድረግ የሚገባቸውን ተግባራት በዝርዝር የሚያመላክት ነውም ብለዋል።

መመሪያውን ለማዘጋጀት ከሁለት ዓመት በላይ እንደፈጀና ከዓለም አቀፍ ጤና ተቋማት ተሞክሮን በመጨመር ቀደም ሲል ከነበረው መመሪያ አዳዲስና የተሻሻሉ አሰራሮችን የያዘ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለመመሪያዎች ትግበራ ጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጾ የየክልሉ የጤና ባለሙያዎች፣ ጤና ቢሮዎች፣ የዩኒቨርስቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የየክልል ተወካዮች በበኩላቸው በህክምና ወቅት መበከልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ መመሪያዎቹን ለመተግበር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ያካሄደው ጥናት አንድ የጤና ተቋም ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ በዓለም ላይ በየዓመቱ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም