በአማራ ክልል በአንድ ቀን 5 ሺህ 115 ዩት ደም ተሰበሰበ

63
ባህርዳር ኢዜአ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ...... በአማራ ክልል ለአንድ ቀን በተካሄደው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ከበጎ ፈቃደኞች ከዕቅድ በላይ ደም መሰብሰቡን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። በቢሮው የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት "ደም ለግሰን ህይወት እናድን" በሚል መሪ ሃሳብ ባለፈው ቅዳሜ በዘመቻ ደም የማሰባሰብ ፕሮግራም ተካሔዷል ። በዚሁ ዘመቻ 3 ሺህ 700 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ሺህ 100 ዩኒት ደም መሰብሰብ እንደተቻለ ተናግረዋል። ለወላድ እናቶችና በአደጋ ምክንያት የደም መፍሰስ ለሚያጋጥማቸው ሰዎች የሚውለው ደም የተሰበሰበው በ10 የደም ባንኮችና በየአካባቢው በተቋቋሙ የደም ልገሳ ጣቢያዎች አማካኝነት ነው ። በእለቱ ከዕቅድ በላይ ደም ሊሰበሰብ የቻለው ዘመቻው ከመካሄዱ ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ ሚዲያው ለህብረተሰቡ ተደራሽ በሆነ መልኩ የተጠናከረ ቅስቀሳ ማድረግ በመቻሉ ነው ብለዋል ። በተጨማሪም የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ምሳሌ በመሆን ደም በመለገስ ያሳዩት በጎ ስራም በህብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃት መፍጠሩን አስረድተዋል። በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ በአብዛኛው የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሆኑም አቶ አንዳርጌ ገልፀዋል። የወገኑን ህይወት ለማትረፍ ህብረተሰቡ በዘመቻው ወቅት ያሳየውን መነሳሳት በየ3 ወሩ ቀርቦ በመለገስ ባህሉ አድርጎ ሊቀጥልበት እንደሚገባም አሳስበዋል። ትርፍ የሆነውን ደም በመለገስ የወገንን ህይወት ከመታደግ የበለጠ ህሊና እርካታ የሚሰጥ በጎ ተግባር የለም ያሉት ደግሞ በዕለቱ በባህርዳር ደም በመለገስ ላይ የነበሩ ወይዘሮ እቴነሽ አዱኛ ናቸው። ደም ሲለግሱ ዛሬ ለአራተኛ ጊዜያቸው ሲሆን ይህን በጎ ተግባር በህይወት እስካሉ ድረስ በየጊዜው ደምን ከመስጠት እንደማይቆጠቡ ገልፀዋል። ወጣት አራጋው አንተሁን በበኩሉ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የትራፊክ አደጋ የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት እየተቀጠፈ ይገኛል። ደም መለገስ ለሞት የተቃረበ የሰው ህይወት መታደግ በመሆኑ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። በክልሉ በ2012 በጀት ዓመት ይሰሰባል ተብሎ ከታቀደው 58 ሺህ 440 ዩኒት ደም ውስጥ ዘመቻውን ጨምሮ እስካሁን 16 ሺህ የሚጠጋ ዩኒት ደም የተሰበሰበ መሆኑን ከክልሉ ደም ባንክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም