መንግስት በአገሪቷ የህግ የበላይነትን በማስከበር የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል- የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

102
ጥቅምት 18/2012 መንግስት በአገሪቱ የህግ የበላይነት በማስከበር የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሳበ። ጉባኤው ባለፈው ሳምንት በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በዚህ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያም ህይወታቸውን ባጡት ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው፤ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶችም መጽናናትን ተመኝተዋል። ንጹሃን ወገኖች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና የህይወት መጥፋትም በሁሉም ኃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለውና ወንጀል በመሆኑም ድርጊቱን አውግዘዋል። የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት “የመንግስት ኃላፊነት ህዝቦቹን በእኩልነት፣ በግልጽነትና በታማኝነት ማስተዳደር በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት መወጣት ተገቢ ነው”። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስም በተመሳሳይ የፍትህ አካላትና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የህዝብ ደህንነትና ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢያሱ ኤልያስ በበኩላቸው መንግስት “ግጭቶች ሳይባባሱ በፍጥነት ማስቆምና የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን ህዝቡ በሚጠብቀው መጠን ሊወጣ ይገባዋል” ብለዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ተወካይ አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው በህብረተሰቡ መካከል ግጭቶችን የሚፈጥሩና የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶም የእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን ድርጊት አውግዘዋል። የመንግስት ኃላፊዎችም ለአገሪቷ ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም እንደሚገባቸውም መክረዋል አባቶቹ። በአገሪቷ ላይ ሁከት፣ አለመረጋጋትና ግጭትን የሚፈጥሩ አካላትንም በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ህብረተሰቡም በተለይም ወጣቶች ለህግ ተገዢ መሆን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። የኃይማኖት አባቶቹ አያይዘውም በፌደራልና በክልሎች ኃላፊዎች መካከል የሚታየው የውጥረት አዝማሚያም ለአገር ሰላምና አንድነት የማይጠቅም በመሆኑ ብሄራዊ መግባባትን ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም