ህብረተሰቡ ደም በመለገስ ያሳየው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሀዋሳ ደም ባንክ ጠየቀ

62
ሀዋሳ ጥቅምት 18/2012 ኢዜአ  ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመከላከል ያሳየውን መልካም ተነሳሽነት አጠናክሮ እንዲቀጥልበት የሀዋሳ ደም ባንክ ጥሪ አቀረበ ። ባንኩ ከእቅዱ በላይ ደም የሰበሰበ ሲሆን የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ  የሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ሰራተኞች በደም ልገሳው ተሳትፈዋል ። የኢንድስትሪያል ፓርኩ ሰራተኞች ባካሄዱት የደም ልገሳ ስነስርዓት ላይ የሀዋሳ ደም ባንክ እንደገለፀው ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ህብረተሰቡ የሚለግሰው ደም ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው። በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የሀዋሳ ደም ባንክ የደም ለጋሾች መልማይ ኦፊሰር አቶ ማቲያስ አንጅሎ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘመቻ ደም የመለገስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ጥቅምት 15 በተካሄደው ዘመቻ 638 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 740 ዩኒት መሰብሰብ ተችሏል። የደም ልገሳ ቀን ከመድረሱ አንድ ሳምንት አስቀድሞ የምዝገባና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት አቶ ማቲያስ ከአራት ሺህ በላይ ደም ለጋሾች በቋሚነት ለመለገስ ምዝገባ እንዳደረጉ ገልጸዋል። ሁሉጊዜ በዘመቻ ማስኬድ አይቻልም ያሉት ኦፊሰሩ “ህብረተሰቡ የደም ልገሳን ባህሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ። አሁን የተመዘገቡት ሰዎች በዓመት ቢያንስ አራት ጊዜ በመስጠት ቋሚ ደም ለጋሽ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። ከኢንዱስትሪያል ፓርኩ ደም ለጋሾች መካከል ወይዘሪት አብነት አርጋው በሰጠችው አስተያየት በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች በወሊድ ወቅት በሚያጋጥማቸው የደም መፍሰስ አደጋ ህይወታቸው እንዳያልፍና እኔም በሴትነቴ ነገ ደም ሊያስፈልገኝ እንደሚችል በማሰብ ጭምር ደም እየለገስኩ ነው ብላለች። የዛሬውን ጨምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ደም መስጠቷን የተናገረችው ወይዘሪት አብነት “ደም በመስጠቴ እኔ በጣም ደስ ብሎኛል ” በማለት ሌሎችም አርአያነቷን እንዲከተሉ መክራለች ። ሌላው ደም ለጋሽ አቶ ናትናኤል ሰብል በበኩሉላቸው በማንኛው ሰዓት ደም በመለገስ የእናቶችና ህጻናት እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎች በሚያጋጥም የደም መፍሰስ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለመታደግ የበኩሌን ደርሻ እያበረከትኩኝ እገኛለሁ ብለዋል ። ደም ሲለግሱ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀው በሚሰጡት ደም የወገናቸውን ህይወት የሚታደግ በመሆኑ ደስተኛነት እንደሚሰማቸው አስረድተዋል ። ለሶስተኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውንና ባደረጉት የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሌሎች ህይወት ለማዳን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኤልያስ ሽታ ናቸው፡፡ “በኔ ደም ሰው መጠቀም ከቻለ እኔ ደሞ መስጠት ከቻልኩ ምንም ችግር የለውም ። ምክንያቱም በምጠጣው ውሀ የሚመለስ ስለሆነ ሁላችንም እንለግስ ” ብለዋል። የኢንደስትሪያል ፓርኩ ባለሀብቶች ማህበር አስተባበሪ ወይዘሪት ትርሲት እንድሪያስ እንዳሉት በዛሬው የደም ልገሳ ስነስርዓት በኢንደስትሪያል ፓርኩ የሚገኙ ባለሀብቶችና የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች የደም ልገሳ ያደርጋሉ። በነገው ዕለትም ሌሎች የፓርኩ ሰራተኞች ልገሳ እንደሚያደርጉና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቶ ሁሉም ፈቃደኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። የፓርኩ የአስተዳደር ሰራተኞች በአብዛኛው በቋሚነት ደም ለመለገስ መስማማታቸውንም ጠቁመዋል። “በሀገር አቀፍ ደረጃ በታወጀው መሰረት እኛም የበኩላችንን ለማድረግ ስምምነት ላይ በመድረሳችን ሁሉም ሰው ደስተኛ ሆኖ እየተሳተፈ ይገኛል” ብለዋል። በደም ልገሳው ላይ በፓርኩ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር ተሳታፊ ሆነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም