የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን ለመከላከል የሚሰጠው ትኩረት እየተቀዛቀዘ መምጣት የበሽታው ስርጭት ዳግም እንዲያገረሽ ምክንያት ሆኗል

160
ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም  (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴና የሚሰጠው ትኩረት እየተቀዛቀዘ መምጣት የበሽታው ስርጭት ዳግም እንዲያገረሽ ምክንያት ሆኗል ተባለ። የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለሰራተኞቹ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል። በዚሁ ወቅት የከተማው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ብርዛት ገብሩ እንደተናገሩት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ላይ በቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በአሁኑ ስዓት ህብረተሰቡ ለበሽታው ያለዉ ትኩረት ተቀዛቅዟል፤ ይህም የመጣዉ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሲደረግ የነበረዉ ድጋፍ በመቀዛቀዙ ነው ብለዋል። በዚህም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት በመስራት ስርጭቱ አሁን ካለበት ደረጃ እንዲቀንስ መደረግ አለበት ሲሉም አሳስበዋል። ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይ ሴተኛ አዳሪዎችን፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች  ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር  ገበየሁ ዋቄ በበኩላቸዉ በተቋማት ውስጥ የተሻለ የስራ ውጤት ለማስመዝገብ በቅድሚያ የሰራተኛዉን ጤንነትና ደህንነት መጠበቅ ይገባል ብለዋል። ጤንነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ሰራተኛ  እንዲኖር የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር   ሰራተኛዉ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረዉ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆም። ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ጤንነታቸው ተጠብቆ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል። ሰራተኞቹ አድልኦና መገለል እንዳይገጥማቸውም አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትም እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም