ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስተካከልና ለመከላከል እየሰራ ነው

64
አዳማ 12/2010 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስተካከልና እንዳይደገሙ ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ለኢዜአ እንደገለፁት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ መምጣቱን ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራና ክትትል አረጋግጧል ። በምርመራው የተረጋገጡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ዋና ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡ በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች አያያዝ ችግርና  በፖሊስ ጣቢያዎች ደግሞ በተጠርጣሪዎች ላይ በሚካሄዱ ምርመራዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል ። ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይንቀሳቀሱና ሰርተው ሀብት እንዳያፈሩ ተፅእኖ የተደረገበትና  በማንነታቸው ፣ በቋንቋቸውና በእምነታቸው ምክንያት ሰብአዊ መብታቸውን የተጣሰበት አጋጣሚዎች መስተዋሉን  ጠቁመዋል ። በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች  በቁጥጥር ስር የሚውሉ ተጠርጣሪዎች በምርመራ ሂደት ድብደባ እንደሚደርስባቸው በምርመራው መረጋገጡንና ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተገኙ የፖሊስ አባላት ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉንም ዋና ኮሚሽነሩ ገልፀዋል ። ኮሚሽኑ በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኘው የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለማክበር ፣ ለማስከበርና ለመጠበቅ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስተካከልና አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ዶክተር አዲሱ ተናግረዋል ። ለዜጎች ሰብአዊ መብቶች መጣስ ዋናው መንስኤ የግንዛቤ ችግር በመሆኑ   ኮሚሽኑ ክፍተቱን ለመሙላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ስልጠናና ምክር ተሰጥቷቸው ከድርጊታቸው በማይታቀቡ አካላት ላይ የህግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል ። የዚሁ አካል የሆነው  በአማራ ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ለማረሚያ ቤቶች ፣ ለፖሊስና ለሚሊሻ ኃላፊዎች እንዲሁም በፌዴራል ደረጃ ለሚገኙ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማእከላት አመራሮች የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል ። የግንዛቤ ማጎልበቻ የስልጠና እድል ካገኙት መካከል የምእራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ላፊ አቶ ሃይሌ ዴቲ በሰጡት አስተያየት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዞናቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚፈፀምበት አጋጣሚ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ የፀጥታ ሃይሎችን የግንዛቤ አድማስ በማስፋት ችግሩን ለመከላከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል ። የአሰላ ከተማ አስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሸምሰዲን መሀመድ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን የዜጎች ሰብአዊ መብት ጥሰት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የፀጥታ ሃይሉን ግንዛቤ በማሳደግ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም