በባሌ ዞን ጥይት ሲያዘዋውር እጅ ከፍንጅ የተያዘው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጠ

128
ጎባ (ኢዜአ) ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በባሌ ዞን ዲንሾ ወረዳ በህገወጥ መልኩ የ“ካርባይን” ጦር መሳሪያ ጥይቶችን ሲያዘዋውር እጅ ከፍንጅ የተያዘ ግለሰብ በአስራትና በገንዘብ ተቀጣ። የዲንሾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ንጉሴ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ በሁለት ዓመት ከሦስት ወር እስራትና በ1 ሺህ ብር እንዲቀጣ የተወሰነው በዲንሾ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። ተጠርጣሪው የተፈረደበት 298 የካርባይን ጥይቶችን ከሻሻመኔ ከተማ ወደ ባሌ ሮቤ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ጭኖ ስጓዝ ዲንሾ ከተማ ላይ እጅ ከፍንጅ በመያዙ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የአካባቢው የጸጥታ አካላት ከህብረተሰቡ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ባደረጉት ፍተሸ ግለሰቡ እጅ ከፍንጅ ሊያዝ መቻሉን ኮማንደሩ አስታውሰዋል። ነዋሪነቱ ምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ ከተማ ቀበሌ 02  የሆነው ጫኮ ሀሰን ጃራ የተባለው ግለሰብ ጥይቶቹን በህገወጥ መልኩ ወደ ባሌ ሮቤ ለማስተላለፍ ሙከራ ሲያደርግ ነው የተያዘው። ኮማንደር ንጉሴ እንዳሉት ተጠርጣሪው ላይ ፖሊስ ምርመራንውን በማጠናከርና ከወረዳው አቃቤ ህግ ጋር በመቀናጀት በዲንሾ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል። ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን ጉዳይ ማጣራቱንና ግለሰቡ መከላከል ባለመቻሉ ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሁለት ዓመት ከሦስት ወር እስራትና በ1ሺህ ብር መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑንም ኮማንደር ንጉሴ አስረድተዋል፡፡ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ገዛኽኝ በየነ በበኩላቸው በቅርቡ ደፍርሶ የነበረው የዞኑ ሰላም በአሁኑ ወቅት ወደተረጋጋ ሁኔታ በመመለሱ አንዳንድ ከተሞች ላይ ተቋርጠው የነበሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል። "የተከሰተውን ግጭት ምክንያት በማድረግ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደዞኑ እንዳይገባ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የክልሉ የፀጥታ መዋቅሮች ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ" ሲሉም አስረድተዋል። እንደ ኮማንደር ገዛኽኝ ገለጻ በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ የነበረው ግጭት የሃይማኖት መልክ እንዲይዝ በማድረግ የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ህገወጥነትን በመከላከል በኩል እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንደር ገዘኸኝ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም