የባህርዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ችግሮች መባባስ አገልግሎቱን እያስተጓጎሉ ነው

66
ባህርዳር ሰኔ 12/2010 የባህርዳር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የመድኃኒት አቅርቦት ዕጥረትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ባለመፈታታቸው የአገልግሎት አሰጣጡ ችግር እያጋጠመው መሆኑ ተገለጸ። ችግሮቹ እንዲፈቱ በባለሙያዎች የቀረበው ተከታታይ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ባለፈው ሃሙስ እና ትላንት ከሁለት ሰዓታት በላይ የአገልግሎት መቋረጥ ተከስቶ ነበር። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ ባየ እንደገለጹት ባለሙያዎች ያነሱትን ጥያቄ ሆስፒታሉ እየፈታ ቢሆንም ከአቅሙ በላይ የሆኑት ባለመፈታታቸው በባለሙያዎች ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል። እንዲፈታ ከጠየቁት መካከል ለሶስት ወራት ሳይከፈላቸው የነበረ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መልስ እንዲያገኝ መደረጉንም አውስተዋል። "ከቀዶ ህክምና መስጫ ክፍሎች ለስራ ምቹ አለመሆን ጋር በተያያዘ አጋጥሞ የነበረውን የጣራ ማፍሰስ ችግር በአፋጣኝ በመጠገን ችግሩን መቅረፍ ተችሏል" ብለዋል። የመድኃኒት አቅርቦት ዕጥረቱ ሊያጋጥም የቻለው በፋይናንስ ዕጥረት ምክንያትና በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ብቻ ሆስፒታሉ ለነፃ ህክምና አገልግሎት የሰጠው 50 ሚሊዮን ብር እስካሁን ባለመተካቱ እጥረቱ ማጋጠሙን አስረድተዋል። አንድ ነርስ በደረጃው ለስድስት ህሙማን ማገልገል ሲገባ አሁን እያገለገለ ያለው እስከ 20 ለሚሆኑ ህሙማን በመሆኑ የስራ ጫና እንዳለ መግለጻቸውን ተከትሎም የሰው ኃይል እንዲሟላ ሆስፒታሉ ለክልሉ ጤና ቢሮ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል። በበጀት እጥረት ምክንያት የሚስተዋለው የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ እንዲሟሉ የተጠየቁ ከ150 በላይ ተጨማሪ ነርሶችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል። ድንገተኛን ሳይጨምር በግማሽ ዓመቱ ብቻ ከ136 ሺህ ለሚበልጡ ተመላላሽ ህሙማን ህክምና መስጠቱን ጠቁመው እንደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበጀት ዕጥረትና ተያያዥ ችግሮች ስራቸውን እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸውም ጠቁመዋል። "ሆስፒታሉ እያጋጠመው ያለውን ችግር በዘዓቂነት ለማቃለልም ቦርዱ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ፣የክልሉ መንግስት የበላይ አመራሮችና ባለሙያዎች ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብዟየሁ ጋሻው በበኩላቸው ባለሙያዎች ከደንብ ልብስ፣ ከመድኃኒት ግብዓት አቅርቦትና ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ማንሳታቸውን ተናግረዋል። በተለይ ለወላዶች ነፃ ህክምና ሆስፒታሉ ያደረገውን ወጭ ቢሮው ለሌሎች ሆስፒታሎች በጀት ሰሞኑን ሲከፋፍል ሶስት ሚሊዮን ብር ለሆስፒታሉ ገቢ መደረጉንም አስረድተዋል። ለጤና መድህንና ለሌሎች ታካሚዎች ሆስፒታሉ ያወጣውን ብር ለማስመለስና እያጋጠመው ያለውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በዚህ ዙሪያ የሆስፒታሉ የቦርድ አመራርና ማኔጅመንቱ ከሰራተኞቹ ጋር ለመወያየት ለነገ ቀጠሮ መያዙን አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም