በራያ አዘቦ ወረዳ 500 ሰዎች የተሳተፉበት አንበጣን የመከላከል ዘመቻ ተካሄደ

71

ማይጨው  ጥቅምት 16 ቀን 2012 በትግራይ ክልል ራያ አዘቦ ወረዳ የመቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ደጋፊዎችን ጨምሮ 500 ሰዎች የተሳተፉበት አንበጣ የመከላከል ዘመቻ ተካሄደ።

ከክለቡ ደጋፊዎች በተጨማሪ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የራያ ዩኒቪርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የማይጨው ችቡድ ፋብሪካ ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

ዘመቻው የተካሄደው ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ጀምሮ በወረዳው የተከሰተውን መንጋ በሰብል ላይ እያደረሰ ያለውን  ጉዳት ለመታደግ እንደሆነ ተገልጿል።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በዘመቻው የተሳተፉ ወገኖች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

መንጋውን ለማጥፋት አርሶ አደሩ ክትትሉን እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

የመቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ደጋፊዎች ደጀን በርሄና ፍትዊ ካህሱ በሰጡት አስተያየት በወረዳው የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ባደረጉት ተሳትፎ እርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በወረዳው የኢርባ ጣቢያ ነዋሪው አቶ ብርሃኑ ኃይሌ ዘመቻው መንጋውን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት  በአዲስ መንፈስ ለመቀጠል ከማድረጉም በላይ ፤በችግራቸው ወቅት ድጋፍ የሚያደርግ ወገን እንዳላቸው ያረጋገገጡበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም