በዘንድሮው ዓመት ሶስት የተለያዩ የካንሰር ህክምና ማዕከላት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ

85
ጥቅምት 15/2012 በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ ካሉት ስድስት የካንሰር ህክምና ማዕከላት መካከል ሶስቱ በዚህ ዓመት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። አሁን አሁን በተለይ በከተሞች የሚኖሩ ሰዎች በብዛት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመያዝ እድላቸው እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። በተለይ በአገር ውስጥ በቂ የህክምና ባለሙያዎች አለመኖራቸውና ህክምናው የሚሰጥባቸው ተቋማትና መሣሪያዎች በቂ አለመሆን ችግሩን እንዳባባሰው ይገለጻል። የበለፀጉት አገራት የካንሰር በሽታን በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው ችግሩን ለመቆጣጠርና የበሽታውን መስፋፋት ለመቀነስ ችለዋል። በአንፃሩ በታዳጊ አገራት ህክምናው በበቂና በተሟላ ሁኔታ አለመገኘት በሽታውን ለመከላከሉና ለመቆጣጠር በርካታ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ የካንሰር በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል። በሰውነት ውስጥ ያሉ ሴሎች ባልተለመደ ሁኔታ በመራባትና በማደግ፣ በኬሚካል፣ በቫይረስ፣ በሲጋራ ማጨስ፣ በፀሐይ ብርሃንና በመሳሰሉ ካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት የሰውነት ሴሎች መጠቃትና መጎዳት የካንሰር ህመም ምክንያቶች እንደሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በኢትዮጵያም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ህክምናው በበቂ ሁኔታ አለመሰጠቱ ደግሞ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። የካንሰር በሽታን በአልትራሳውንድ፣ በሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ፣ በኤክስሬይና ቦን ስካን በተባሉ የምርመራ ዘዴዎች ማወቅ ይቻላል ይላሉ። ለካንሰር በሽታ ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል ቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ቴራፒና፣ ባዮሎጂካል ቴራፒ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ዓለም አቀፉ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ (IARC) እንደ አውሮፓዊያኑ በ2012 በኢትዮጵያ ባደረገው ጥናት፤ 60 ሺህ 700 በላይ የካንሰር ህሙማን መኖራቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ መካከል 19 ሺህ 654ቱ ወንዶች ሲሆኑ 41 ሺህ 95 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ያመላክታል። በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት አማካሪ ዶክተር ብርሃነ ረዳኢ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት የካንሰር ህክምና የሚሰጡ ማዕከላትን እያስገነባ ይገኛል። የካንሰር ህክምና ማዕከላቱ ግንባታ በጅማ፣ በሀረማያ፣ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ ጎንደርና በአዋሳ የሚከናወኑ ናቸው። ለእነዚህም ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስድስት ዘመናዊ የጨረር ወይም የሬዲዮቴራፒ መሳሪያዎች ግዢም ተካሂዷል። በአሁኑ ወቅትም በጅማ፣ በሀሮማያ እና በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የህክምና ማዕከላት ግንባታቸው በዚህ አመት ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል። ይህም የተጠቃሚዎችን ከፍተኛ መንገላታትና የረጅም ጊዜ የህክምና ቀጠሮ የሚያስቀር እንደሚሆን ታምኖበታል። እንደ ህክምና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ከሆነ፤ በካንሰር ህመም የተያዙ ሰዎች ታክሞ የመዳን ዕድላቸው እንደ ህመሙ ዓይነት፣ ሕመሙ የሚገኝበት ደረጃ፣ የታማሚው ሰው ዕድሜና ህክምናው በተሟላ ሁኔታ መስጠት አለመስጠቱ ላይ የተወሰነ ነው። ዓለም አቀፉ የካንሰር ድርጅት በ2012 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ በዓለም በየዓመቱ 7 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወቱ የሚያልፍ ሲሆን 11 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው ይያዛል። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ህመም ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ። በየዓመቱ በካንሰር በሽታ የሚያዘው ሰው ቁጥርም 16 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም