የህጻናትን ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ገለጸ

58
ኢዜአ ጥቅምት 15/2012 ዓ/ም መንግስት የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ህብብረተሰቡን በማሳተፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ገለጸ። በህጻናት ፍለሰትና በጎዳና ላይ በሚያጋጥማቸው ችግሮች መፍትሄዎች ዙሪያ የሚመከር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል። በሚኒስቴሩ የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሙድ እንዳሉት  በሁለ ክልሎች  ህብረተሰቡን ያሳተፈ  የማህበረሰብ አቀፍ የህጻናት እንክብካቤና ደህንነት ጥምረት በመመስረት የመረዳዳትና የመደጋገፍ በጎ ባህል እንዲጎልብት ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም ህብረተሰቡ በቡድንና በተናጠል ህጻናትን ተረክቦ በማሳደግ፣ በማስተማርና የቀጣይ ህይወታቸው እንዲስተካከል የተደረገው ጥረት ፍሬ ማሳየቱን አመልክተዋል። ሆኖም ድህነትና የቤተሰብ ሁኔታ በላይ አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ወደ ከተማ የሚፈልሱ የሚወጡ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ህጻናት የሚፈልሱባቸውን አካባቢዎች በመለየት ለፍልሰት ምንጭ የሆኑ  ችግሮችን ለይቶ በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል። መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ  የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ አሁንም  ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ወይዘሮ አለሚቱ ገልጸዋል። በሀገሪቱ  ዋና ዋና ከተሞች 150ሺህ ህጻናት በጎዳና ላይ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የገለጹት ደግሞ  በሚንስቴሩ የህጻናት ዘርፍ ባለሙያ  አቶ ዮሃንስ ሰንደቁ ናቸው። በኢትዮጵያ ያለው የቤተሰብ ትስስር ጠንካራ በመሆኑ አራት ሚሊየን ህጻናት በቅርብ ዘመዶች ደህንነታቸው ተጠብቆና እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንደሚያድጉ አመልክተዋል። ለህጻናት ፍልሰት የወላጆች ሞት፣ ድህነትና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች  መሆናቸውን ጠቁመው የጉልበት ብዝበዛ፣ የሱስ ተጋላጭነት፣ መደፈርና የመሳሰሉ በጎዳና ላይ የሚያጋጥሙ  ፈተናዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። "መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም ጎዳና የወጡ ህጻናትን ወደ ቅርብ ቤተሳባቸው መመለስና ሊፈልሱ የሚችሉትን ባሉበት በመደገፍ ምንጩን እያደረቁ መጓዝ ያስፈልጋል "ብለዋል። የባህርዳር ከተማ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አምሳል ካሳው በበኩላቸው በከተማቸው 900 የሚሆኑ ህጻናት ጎዳና ወጥተው ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተደረጋ የዳሰሳ ጥናት በርካታ ህጻናት ፈልሰው ወደ ከተማቸው የመጡት ከደቡብና ከሰሜን ጎንደር  እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም  እንደሆነ ጠቁመዋል። ኃላፊዋ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ዓመታት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሶስት ወራት  ስልጠና በመስጠት ወደ ነበሩበት አካባቢዎች ለመመለስ ቢሞከርም ተመልሰው መጥተዋል። ለዚህም በአካባቢያቸው ያለው አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ህጻናቱን ከተረከቡ በኋላ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ካለማድረግ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው " በቀጣይ ይህን ችግር መፍታት ይገባል "ብለዋል። ለዚህም የአሁኑ  የንቅናቄ መድረክ በክልሉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ በመሆኑ በቀጣይ ችግሩን አነስቶ በመግባባት ውጤታማ ስራ ለማከናውን እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በንቅናቄ መድረኩ በአማራ ክልል የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም