በኢትዮጵያ የሄማቶሎጂ እና ኦንኮሎጂ ማህበር ተመሰረተ

86
ኢዜአ ጥቅምት 15/12 ዓ/ም በኢትዮጵያ በካንሰር ህመም ላይ ጥናትና ምርምሮችን የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ የሄማቶሎጂ እና ኦንኮሎጂ ማህበር ተመሰረተ። የአዓም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ከስምንቱ የአንዱ የሞቱ ምክንያት የካንሰር ህመም ነው። በየዓመቱ በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቱን የሚያጣው ሰውም በኤች.አይ.ቪ.ኤድስ ከሚሞተው በእጥፍ እንደሚበልጥ ይጠቁማል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ካሉት የካንሰር ታማሚዎች መካከል የህክምና አገልግሎት የሚያገኙት 10 ሺህ የሚደርሱ ሲሆን ይህም ከታማሚዎች ቁጥር 15 በመቶው ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የሄማቶሎጂ እና ኦንኮሎጂ ማህበር መመስርትም በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የካንሰር ህመም በተገቢው ሁኔታ ህክምና ለመስጠት እንዲያስችል ታስቦ ነው ተብሏል። የማህበሩ ፕሬዘደንት ዶክተር አይናለም አብርሃ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የካንሰር ህመም በፊት ከነበረበት እየጨመረ ከመሄዱ አንጻር አሁን ላይ በቂ የህክምና አገልግሎት የለም። ማህበሩ ከመንግስት ብሎም አገር ውስጥ ካሉና ከዓለም አቀፍ ማህበራት ጋር በጋራ በመሆን ለህክምና ባለሙያዎች ስልጠናዎችን ይሰጣል ብለዋል። በካንሰር ህመም ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይሰራልም ነው ያሉት። በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት አማካሪ ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ወደ ኋላ የቀረ የህክምና ዘርፍ ነው። ለህክምናው የሚያስፈልገው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መሆንና ብቁ የሰው ሃይል እጥረት ዋነኛ ችግሮች ናቸው ብለዋል። በዚህም ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችል የሰለጠነ ባለሙያ በማፍራት ብሎም ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋማት ዘግይተው የሚሄዱ በመሆናቸው ጉዳት የሚደርስባቸው ሲሆኑ ተከታታል ህክምና በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይጠይቃልም ነው ያሉት። የሰው ሃይል ለማሟላት ከዩኒቨሲሪዎችና ከማህበሩ ጋር በመሆን የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል። “ሄማቶሊጂ” ማለት በደም ዙሪያ የሚያጠና የህክምና ሙያ መስክ ሲሆን ቃሉም “ሄም” ከሚለው የግሪክ ቃል የተወሰደ መሆኑ ይነገራል። ትርጓሜውም “ደም” የሚለውን ቃል የሚተካ ሲሆን “ሄማቶሎጂ” ማለትም በደም ውስጥ ሊከሰቱ ስለሚችሉ በሽታዎች የሚያጠና እንደማለት ነው። ኦንኮሎጂ ማለትም ስለ ካንሰር ህመም የሚያጠና የሞያ መስክ ነው። እንደ አጠቃላይ  “ሄማቶሎጂስት እና ኦንኮሎጂስት” ማለት የደም ካንሰር ህክምና ባለሙያዎች ማለት ሲሆን እንደ ሉኩሚያ፣ ሊምፎማ እና ሚሎማ የተሰኙ የደም ካንሰር ህመሞችን ያክማሉ። በዛሬው እለት በይፋ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የሄማቶሎጂ እና ኦንኮሎጂ ማህበር 60 አባላትን የያዘ ነው።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም