ደም በመለገስ ህይወት በመታደጋቸው መደሰታቸውን ለጋሾች ገለጹ

55
ባህርዳር/ ሰመራ ኢዜአ ጥቅምት 15/2012፡- ደም በመለገስ ህይወታቸውን ሊያጡ የነበሩ ወገኖችን መታደጋቸው እንዳስደሰታቸውና ባህልም ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን በባህርዳርና ሎጊያ ከተሞች የሚኖሩ ለጋሾች ገለጹ። "ህይወትን ለህይወት ደም በመለገስ ህይወት ያድኑ " በሚል የደም ልገሳ መርሃ ግብር በባህርዳር እና ሰመራ- ሎጊያ ከተሞች እየተካሄደ ነው። በባህርዳር የዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ግርማ ጌቴ በሰጠው አስተያየት ዛሬ የለገሰው ደም ለሁለተኛ ጊዜው እንደሆነ ተናግሯል። ደም ለመለገስ ያነሳሳውም ቤተሰብ ታሞበት ሆስፒታል በነበረበት ወቅት በመኪና አደጋ የተጎዳ ሰው መጥቶ ደም እንደሚያስፈልገው ሰጠየቅ በፈቃደኝነት ሰጥቶ ህይወቱን ማትረፍ በመቻሉ እንደሆነ ገልጿል። "የሰጠሁት ደም ህይወቱን ሊያጣ የነበረን ሰው ማትረፍ ከቻልኩ በየሶስት ወሩ አንድ ዩኒት ደም በመለገስ ብዙ የተቸገሩ ህመምተኞችን ለማዳን በመወሰኔ ዛሬ ለመስጠት በቅቻለሁ" ብሏል። ሌላኛው የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌር  አቶ ጥበቡ ተገኝ በበኩላቸው ደም ለመለገስ የነበረው ፍላጎተ ከስራው  ባህሪ አኳያ ሳይሳካለት ቢቆይም ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በመለገሳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። በወሊድና በትራፊክ አደጋ በርካታ ሰዎች በሚያጋጥማቸው የደም መፍሰስ ህይወታቸውን ሲያጡ ስለሚመለከቱ  ደም ለመለገስ እንደተነሳሱ ገልጸዋል። "በምለግሰው ደም ልትቆረጥ የደረሰችን እስትንፋስ ዳግም እንድትቀጥል ከማድረግ የበለጠ የሚያስደስተኝ ነገር የለም "ያለችው ደግሞ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፌቨን ተሾመ ናት። ሌሎች ጓደኞቿ እንዲለግሱም እንደምትመክርና ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ መለገሳን ገልጻ  በቀጣይም በየሶስት ወሩ ሳታቋርጥ  እንደምትሰጥ ተናግራለች። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ በበኩላቸው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ዛሬ ባህርዳርን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መርሃ ግብርም  3ሺህ 448 ዩኒት  ደም ለመሰብሳብ ታቅዷል። በተመሳሳይ በአፋር ክልል ሎግያ ከተማ በደም ልገሳ መረሃ ግብር ከተሳተፉት መካከል አቶ አሊ ሁሴን እንዳሉት የዛሬን ጨምሮ ደም ለሰባት ጊዜ ለግሰዋል። ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የራሱን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር ኝ በደም እጦት ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖቹን መርዳትን ባህሉ አድርጎ ቢቀጥል ፍላጎታቸው  መሆኑን ተናግረዋል። ሌላው በዚሁ ከተማ ደም ሲለግሱ የነበሩት አቶ ኢብራሂም አደም በበኩላቸው በተሰማሩበት  የህክምና ሙያ ብዙ ጊዜ ሰዎች በደም እጦት ምክንያት እንደሚቸገሩ ገልጿል። በዚህም ዛሬን ጨምሮ ለዘጠነኛ ጊዜ  ደም መለገሱን ገልጾ  በህብረተሰቡ ዉስጥ ስለደም መስጠት ያለዉን አመለካከት ለመቀየር ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መጠናከር እንዳላበት አመልክቷል። የሰመራ ደም ባንክ ኃላፊ አቶ አወል በአካባቢው ህብረተሰብ ደም የመለገስ ባህሉ ቢሻሻልም ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል። የአፋር ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ  ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ እንዳሉት ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ባሉት የደም ባንኮች ከአካባቢው ህብረተሰብ ደም በመሰብሰብ በአቅራቢዉ ለሚገኙ ሆስፒታሎች የማቅረብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው። በክልሉ የሀገር-አቀፉ ንቅናቄ አካል በሆነው የዛሬው ፕሮግራም  290 ዩኒት ደም በአዋሽ ሰባት ኪሎና በሰመራ-ሎግያ ከተሞች ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም