በመጪው ቅዳሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጋና እና የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ነው

75
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያካሄዷቸው ባሉት የለውጥ እርምጃዎችና ላመጧቸው ተጨባጭ ለውጦች የፊታችን  ቅዳሜ የምስጋና እና የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መታሰቡን የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ። በመጪው  ቅዳሜ ሰኔ16 2010  ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፉ እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ዛሬ ለአገር ውስጥና ለውጪ መገናኛ ብዙሃን በድጋፍ ዙሪያ  መግለጫ ሰጥቷል። የሰልፉ ዋና ዓላማ በአገሪቷ አሁን ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ በማበረታታት እውቅና ለመስጠት ያለመ ሲሆን ኢትዮጵያውያን መሪያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የሚያመሰግኑበትና በቀጣይ ለሚሰሯቸው ሥራዎችም ከጎኑ ለመሰለፍ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልፁበት ነው ተብሏል። የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት አቶ ጉደታ ገለልቻ፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ አቶ ስዩም ተስፋዬ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በጋራ በሰጡት በዚሁ  መግለጫ፤ ሰላማዊ ሰልፉ ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎናቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያለ ልዩነት የሚሳተፉበት ይሆናልም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ  በአገሪቷ ህዝቦች ዘንድ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቁ እርምጃዎችን በመውሰዳቸውና ምልክቶችን በማሳየታቸው "የለውጡ ሂደት እንዳይስተጓጎል ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል" ሲሉም ገልፀዋል። በመሆኑም የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ16 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፉ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በምስጋና እና በድጋፍ ሰልፉ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዙሪያ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር 'ራዲየስ' የሚገኙ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስተባባሪዎቹ ከወዲሁ ግምት ሰጥተውታል። ሰላማዊ ሰልፉ ከየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አመለካከት፣ ከብሄር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋ እና ሌሎች አመለካከቶች የፀዳ መሆኑን የገለፁት አስተባባሪዎቹ፣ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌሎች አመለካከቶች በሰልፉ ላይ ማንፀባረቅ እንደማይቻል አስገንዝበዋል። የአሁኑ ሰልፍ በአዲስ አበባ ብቻ የተጠራ ቢሆንም በቀጣይ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የማድረግ እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል። የድጋፍ ሰልፉ ቅዳሜ ቢጠራም አስካሁን ባለው መረጃ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፍቃድ ጠየቁ እንጂ ከሚሰጠው አካል እስካሁን ያገኙት ፍቃድ እንደሌለ ገልፀው "እንከለከላለን" የሚል እምነት እንደሌላቸው ግን አስረድተዋል። ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግም በየወረዳው ንዑስ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ አገሪቷ ቀጣይ ሰላሟ እንዲረጋገጥ መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ጠይቀዋል። ለሰልፉ ስኬት እና በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግና እጅ ለእጅ ተያይዞና ተደምሮ አገሪቷን ለመቀየር ርብርብ እንዲደረግም ጠይቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም