የፖሊስ ሰራዊት ና ግልጋሎቱ

913

በቁምልኝ አያሌው እና ቀበኔሳ ገቢሳ (ኢዜአ)

ለአንድ አገር ህልውና ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ተቋማት መካከል የጸጥታ ዘርፍ  ወሳኙና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ነው። የአገር ዳር ድንበር ተከብሮ፣ ዜጎጎች ያለስጋት በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በማድረግ ደረጃ የጸጥታ አካላት በማንም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል። ከጸጥታ አካል ዋና ዋና ተቋማት  የመከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ ሰራዊት እና የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል። በተልይም ፖሊስ ከሁሉም በላይ የህግ የበላይነትን በማስከበር ላይ አትኩሮ ይሰራል።

በአለማችን የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎትና ፅንሰ-ሀሳቡ (ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) እ.ኤ.አ. በ1927 የለንደን ዘመናዊ የፖሊስ ሰራዊት ሲመሠረት የከተማዋ የፖሊስ መሪ የነበሩት ሠር ሮበርት ፒል የመነጨ ሃሳብ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚሁ ባለውለታና የሰላም አምባሳደር የፖሊስና ህዝብን መስተጋብር ሲያስረዱ ‘ፖሊስ ህዝብ ነው፤ ህዝብም ፖሊስ ነው’ በማለት እንደመነሻ የማብራሪያ ሃሳብ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው። ይህ ሃሳብ የፖሊስ አሰራር እና ዘዴ ተደርጎ በደንብ ስራ ላይ መዋል የጀመረው ግን እ.አ.አ በ1979 ሄርማን ጎልደስቲን የተሰኙ የሃሳቡ ተጋሪ ግለሰብ ሃሳቡን አስፋፍተው ወደ ችግር ፈቺ የፖሊስ ተቋምነት መቀየር ከቻሉ ወዲህ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እ.አ.አ. ከ1980 በፊት በነበረው ሂደት ውስጥ በተለይ በሰሜን አሜሪካ በህብረተሰቡ ላይ ወንጀልና ብጥብጥ በእጅጉ እየተስፋፋ በመምጣቱ የተደራጀ የማህበረሰብ ፖሊስ አስፈልጎ ነበር፡፡ የፖሊስ ኃይል እነዚህን ችግሮች ብቻውን መቆጣጠርና መፍታት እንዳልቻለ በተጨባጭ ግልፅ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በ1980ዎቹ አዲስ የፖሊስ አገልግሎት ሐሳብና ዘዴ ሥራ ላይ መዋል እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይኸው አዲሱ የፖሊስ አገልግሎትም ‘የማህበረሰብ ፖሊስነት’ ወይም ‘ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ’ ስያሜ እንዲሰጠው ሆኗል፡፡

የሃሳቡ መነሻነትም ማንኛውም የፖሊስ ስራ በተለይም ወንጀልን መከላከል ያለ ህብረተሰብ ተሳትፎ ግቡን ሊመታ እንደማይችል ግንዛቤ የተያዘበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ፍልስፍና በዋናነት በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ እነሱም፡ አብሮ መስራት ፣ ችግር መፍታት እና ለውጥ ወይም የድርጅት ሽግግር  ሲሆኑ፤ ይህ አሰራር ተግባራዊ መሆን በጀመረባቸው አከባቢዎችና ሃገራት ውጤታማ ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ በብዙ የዓለም ሀገራት ተግባራዊ ሆኗል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የፖሊስ ሰራዊት ወይም የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ቅድመ-ታሪክ ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ  በ1905 ዓ.ም የመጣ ፅንሰ-ሃሳብ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዱናል።  በወቅቱም ፖሊስ ወይም ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ በአዲስ አበባ ደረጃ የአራዳ ዘበኛም እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከ1905 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1934 ዓ.ም የሃገራችን የፖሊስ ሃይል ይመራ የነበረው በውጭ ወራሪ ሃይሎች እንደነበር በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህ የሆነበት አብይ ምክንያትም በወቅቱ የነበሩ የፖሊስ ሰራዊት አባላት በጣሊያን ወራሪ ሃይሎች ስራቸውን ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊስ ተቋምና ሰራዊት ዘመናዊ የሆነ አሰራር እንዲኖረው የተደረገው ደግሞ ከ1934 ዓ.ም ወዲህ በአዋጅ 6/1934 ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ ቀስ በቀስም ከአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ መመስረት ጋር ተያይዞ ዘመናዊ እየሆነ በሳይንሳዊ እውቀትና ክህሎት እየታገዘ መጣ፡፡  በ1934 ዓ.ም የመጀመሪያው የፖሊስ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ በፖሊስ ተቋምና ሰራዊት መመራት መጀመራችን ያሳያል ባይባልም ህገ ስርዓቱ መደንገጉን ግን መረጃዎች ያሳዩናል፡፡

ይህ የፖሊስ አዋጅ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ‘የወራሪ ጠላት ግዛት’ ከሚል ስያሜ  ወደ ‘የኢትዮጵያ ንጉስ ፖሊስ ኃይል’ እንደተለወጠ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኃይል ከ1934 እስከ 1967 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ አሰራሩ በዋናነት በአንድ እዝ ሰንሰለት ከማዕከል ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም በከፊል ይንቀሳቀስ የነበረውን የመከላከያና የጦር ግንባር በሂደት ወደ ፖሊስ ሙያነት እየተለወጠ እንደመጣ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖሊስ አሰራርና የህብረተሰብ ተሳትፎ ደካማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሳሪያ የታጠቀ ህዝብ (ሚሊሻ) የፀጥታ ዘርፉን ለማስጠበቅ ተሳትፏቸው የጎላ ነበር፡፡

የህብረተሰቡን የወንጀል መከላከል ተሳትፎ ለማሳደግ ከነበሩት ሙከራዎች ውስጥ አንዱ ፖሊስና እርምጃው በሚል የሚዘጋጀውን በራሪ ወረቀት በመጠቀም ስለ ወንጀል መከላከል የሚያስተምር የፖሊስ ክፍል አንዱ ተግባር እንደነበርም የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የወንጀል ምርመራ ሂደቱን ከህብረተሰቡ ተሳትፎ በማከል አውጫጭኝ የሚባል የምርመራ ዘዴ እንደነበርም ፀሃፍቶች ያስረዳሉ፡፡ የሃገራችን የፖሊስ ሰራዊት ተቋም አደረጃጀትና ስልጠና ስትራቴጂክ እቅድ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግበት እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የቀጠለ ሲሆን የሚሰጡ ስልጠናዎችም ቢሆኑ ከፖሊስ አሰራር ጋር ብዙም ዝምድና ያልነበራቸውና ከፖሊስ ሳይንስ ጋር በተቃራኒ የሆኑ ነበሩ፡፡ ከቆይታ በኋላም በ1967 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ-ስላሴ አስተዳደር በወታደራዊ ደርግ ከተወገደ በኋላ ወታደራዊው መንግስት ስልጣን ሲጨብጥ የፖሊስ ሰራዊት በሚኒሻ መተካት አለበት፤ የለበትም የሚል ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በዚህ ግራ የተጋባ አስተሳሰብ ውስጥም አብዛኛው ሙያዊ የፖሊስ ሃይል ወደ ጦር ሰራዊትነት ተቀየረ፤ ጥቂት የሚባሉ አባሎች ደግሞ ለምርመራ በሚል ወደ ማዕከላዊ በመወሰዳቸው ሳቢያ አብዛኞቹን የሰለጠኑና ሙያዊ ብቃት ያላቸው አባላትን እንዲያጣ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከተለያዩ ጽህፎች የተገኙት መረጃዎች እንደሚሳዩት ከሆነ ይህ አሰራርም ፖሊስን የታወቀ ስልጣን እንዳይኖረው በማድረግ የፖሊስ ስልጣን ዜጎችን የማሰር፣ የመመርመር፣ የማሰቃየትና የመግደል በማድረግ ስልጣኑም ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ለቀበሌ ወይም ለየአካባቢ ወታደሮች እንዲሰጥ ተደርጎ ነበር፡፡ የፖሊስ አባላት ምልመላ ሂደትም ቢሆን ሲከናወን የነበረው እሾህን በእሾህ በሚል ፍልስፍና ስራና ገቢ የሌላቸው እንደወንጀለኛ የሚቆጠሩ ሰዎች ይመረጡ ነበር፡፡ እነዚህ ለስራው ፍቅርና ህዝቡን ለማገልገል ቁርጠኝነት የሌላቸው ይልቁንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለማስወገድና በመንግስትም የተጣለባቸውን የብሔራዊ ውትድርና ግዴታ ለማምለጥ ሲሉ የተቀጠሩ ነበሩ፡፡ መንግስትና በወቅቱ የነበሩ የፖሊስ አመራሮች በፈጠሩት የፖሊስ ምልመላ ስህተት የስራ አፈፃፀሙ ወደ ባሰ ችግር እንዲሸጋገር አድርገውት እንደነበረም መረጃዎች ያሳያሉ።

የፖሊስ ኃይል በየጊዜው እየቀነሰ ከመሄዱም በላይ በዝምድና መስራት፣ ስልጣንን ያለአገባብ መጠቀምና ብልሹ ውስጣዊ የፖሊስ አደረጃጀት ተዳምረው በወቅቱ በነበረው የፖሊስ ስራ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ በጊዜውም አብዛኛው የፖሊስ ኃይል ያለ ስራ የተቀመጡ ነበር ይባላል፡፡ በአጠቃላይ ከ1967-1983 ዓ.ም ድረስ ያለውን የፖሊስ ተቋም አደረጃጀትና አሰራር ስንመለከት ምንም አይነት መመሪያና ስትራቴጂ ካለመኖሩ ባሻገር ፀረ-ዲሞክራሲ፣ በማዕከላዊ አደረጃጀት የታጠረና አምባገነን፣ ፓራ-ሚሊተሪ እና ከህዝብ የተነጠለ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሲያጋጥሙ የነበሩ ወንጀልን ለመከላከል በየቀበሌው የነበረው ህዝብና የአካባቢው ሚሊሻ ተደራጀተው ይሳተፉ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም  ወታደራዊ መንግስት ከስልጣን መንበሩ ከተወገደ በኋላ የፖሊስ አደረጃጀት ስርዓቱ ያልተማከለ አሰራር መርህን መሰረት በማድረግ ክልሎች የየራሳቸው ፖሊስ እንዲኖራቸው ተደርጎ ማንኛውንም ዓይነት የፀጥታ ጉዳይ ለክልሎች እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ይህ ያልተማከለ የፖሊስ አደረጃጀት አሰራር ስርዓት በዋናነት ዋና ዓላማ ፖሊስ የሲቪል ማህበረስብ አገልጋይ እንዲሆን ነው፡፡ ሌላው የፖሊስ ለውጥ ደግሞ የስልጠና ለውጥ ሲሆን ስልጠናው ከወታደራዊ ፖሊስነት ወደ ሲቪል ፖሊስነት የሚቀይር አድርጎታል፡፡ ይህ ለጋራ ደህንነት አስፈላጊ የሆነው ተቋም ፖሊስ  በነፃነት ሰበብ የሌሎችን መብት እንዳይጋፋ ጥበቃ ያደርጋል፤ ወንጀልን ይከላከላል፡፡

ፖሊስ የሌሎች ግለሰቦች ወይንም የወል ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ አገር፣ መንግሥት፣ መሥሪያ ቤቶች የመሳሰሉት ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደረስ ይከላከላል፤ ጉዳት ሲደርስም የጉዳት አድራሹን ማንነትና የድርጊቱን አፈጻጸም የሚያሳይ ማስረጃ ያፈላልጋል፤ ወይንም የወንጀል ምርመራ ያደርጋል፡፡ ፖሊስ እንደ ተቋምም በዋናነት ሁለት ተልዕኮዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት መከላከልና ከተፈፀመ በኋላ ምርመራ ማካሄድ ናቸው፡፡  የፖሊስ አስፈላጊነት ጥያቄ ባያስነሳም መደበኛ ስራዎችን በሚያከናውንበት ወቅት በሚወስዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጋለጡ ስለሆነ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይከሰቱ የፖሊስ አባላት ወደ ስራ ሲገቡ የተለያዩ የምልመላ መስፈርቶችን በማለፍ ነው፡፡

በዚህም ሃገራት በተናጠል ለራሳቸው ብሎም በጋራ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሠራሩን ለማቅናት ሲሉ በርካታ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ ከነዚያ ውስጥ አንዱ የፖሊስ ምልመላ መሥፈርት በዋናነት እንደመነሻ የሚነሳ ጉዳይ ያደርገዋል፡፡  በሃገራችንም ቢሆን ፖሊስ ለመሆን ፍላጎት ያለዉ ማንኛዉም ሰዉ፤ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ለፌዴራልና ለክልሎች ሕገ-መንግስት ታማኝና ተገዥ የሆነ፣ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት የሚያምን፣ በሃይማኖቶች እኩልነት የሚያምን፣ መልካም ሥነ-ምግባር ያለው፣ ያላገባና ልጅ ያልወለደ፣ ዕድሜዉ ከ18 ዓመት ያላነሰ እና ከ25 ዓመት ያልበለጠ፣ የማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ፣ ቢያንስ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀ፣ ለፖሊስነት የሚያበቃ አካላዊ ብቃትና የተሟላ ጤንነት ያለው፣ የወንጀል ቅጣት ሪከርድ የሌለበት እና የሚሰጡትን የመግቢያ ፈተናዎች ያለፈ መሆን እንዳለበት የኢፌዴሪ ፌዴራል ፖሊስ መተዳደሪያ ደምብ መረጃ ያሳያል።

አሁን አሁን ግን በአገራችን እየተስተዋሉ ያሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ስልጠናውን አጠናቀው የሚወጡ የፖሊስ አባላት ከሞላ ጎደልም ቢሆን ስልጠና ጨርሰው ሲወጡ እነዚን መስፍርቶች አሟልተው ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል።በተለይም ለምልመላ ያመለከተውን ሰው ባህሪውንና ስብዕናውን በጥልቅ ለመረዳት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በምልመላና ስልጠና ሊሳተፉ ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነም በኋላ ወንጀል በመከላከልም ይሁን በምርመራ ወቅት የሰብዓዊ መብትን እንዳይጥሱ በየጊዜው በቂ ሥልጠና ቢሰጥ መልካም  እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

እንደ ሌሎች ሙያዎችም የፖሊስ የሥነ ምግባር ደንቦችም አሉ፡፡ በርካታ አገሮች የሥነ ምግባር ደንቦቹ በትክክል መተግበራቸውን የሚከታተል በፖሊስ ተቋሙ ውስጥም ሆነ ውጭ የሚገኙ ተቋማትና የተዘረጉ የአሠራር ስርዓቶችን ክትትል ማድረግ እና ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫ ማሳየትም ያስፈልጋል፡፡ ምክኒያቱም አንድ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ዳኛ  ወይም ሌላ ባለሙያ የሙያውን ሥነ-ምግባር የሚተላለፍ አድራጎት ከፈፀመ ተጠያቂነት እንዳለበት ሁሉ ፖሊስም በወንጀል፣ በዲስፕሊንና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂና ኃላፊነት ሊኖርበት ስለሚገባ ይኼው አካሄድ እየዳበረ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አንዳንድ አባላቶች ግን ለገቡት ቃል ተገዥ ናቸውን? ይህን ጥያቄ ያነሳነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመድናችን አዲስ አበባ በፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል እየተስተዋለ የሚገኘው አለመግባባት ከግጭት እስከ ህይወት ማለፍን አስከትሏል፡፡ ለምሳሌ በያዝነው አመት  ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም  ምሽት በአዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ 2 የፌደራል ፖሊስ አባላት ህይወታቸው ማለፉንና 4ቱ መቁሰላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሙዩኒኬሽን አስታውቆ ነበር። በ2011 ዓ.ም በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በጥበቃ ላይ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ባልደረቦች መገዳደላቸው በዛው አመት በቦሌ በሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቶች መኖሪያ ግቢ ተመሳሳይ ድርግት መከሰቱ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋልል ።

ከኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሠረታዊ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የሆነው በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ  ማህበረሰብ በጋራ የመገንባት ዓላማ ከግብ የሚደርሰው የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበራቸው ሲረጋገጥ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ለፖለቲካ ፍጆታ እንዲውል አቅደው በተለያዩ መስኮች እና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው የኖሩትን የሀገራችንን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ውስጥ ግጭቶችን በመቀስቀስ ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የንብረት ውድመት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲደርስ እያደረጉ ይገኛል መንግስትም እነዚህን  አካላትን የሕግ የበላይነትና የህዝባችንን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል በኮሚሽኑ ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል እየተባለ ሲነሳ ይሰማል።

የፖሊስ ኮሚሽኑ ከህዝብ ጋር በመሆን  የህግ የበላይነትን ለማስከበር ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት በጥናትና ምርምር፣ ከአዝማሚያ ትንተና እና ከህዝብ አስተያየት በመነሳት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በማምከን የቅድመ መከላከል ስራ መስራት ይኖርበታል። ከዚህ አልፎ ወንጀል ከተፈፀመ የወንጀል ድርጊቱን በማጣራት ማስረጃ በማሰባሰብ በጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከአቃቤ ህግ አካላት ጋር በመተባበር እስከ መጨረሻው ጉዳዩን በመከታተል ፍርድ እንዲሰጥ ማድረግ ይኖርበታል።

በህዝቦች ትግልና ግፊት የመጣው ለውጥ ሀገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር፣ ለሀገራችን ዘላቂ ብልጽግና መሠረት የሚጥል፣ የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና ህዝቦች በኮሚሽኑ ላይ የሚያነሷቸውን  ቅሬታዎች በመፍታት እና የማይቋረጥ ቋሚ የአሰራር ሥርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ህዝቡን በታማኝነት መገልገል ይገባል። በቅርብ ጊዜ መንግሥት የሕግ አስፈፃሚ አካላትን ተደራሽነት እና ብቃት ለማሳደግ አስፈላጊ እርምጃዎችን ወስዶ ዘመናዊ የፖሊስ አደረጃጀት ለመገንባት እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የፖሊስ ቁልፍ ሚና የወንጀል ተግባር በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዳይፈፀም መከላከል ነው፡፡

በፖሊስ ሥነ ምግባር ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ “መልካም እና ሃቀኛ ምግባር” መላበስ ነው። ይኸው “የፖሊስ ሥነ ምግባር” የሚለው ቃል በፖሊስ መኮንኖች ምግባር፣ ባህሪ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የእሴቶች ኮድ ስለሆነ ነው። ፖሊስ በህብረተሰቡ ውስጥ የወንጀል ድርጊቶችን በመመርመር እና በመፍታት ማህበራዊ ስርዓትን ይጠብቃል፡፡ በጎረቤቶች ወይም በቤተሰብ አባላት መካከል አለመግባባት በሚከሰትበት ወቅት ጥሩ የድርድር ችሎታዎች ተጠቅሞ መፍታት ይችላል። ይህ ችሎታ የፖሊስ ኃላፊነቶችን ለመወጣት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ህብረተሰቡ በአክብሮት ከተያዘ ሁሉንም አካባቢ መልካም ማድረግ ይቻላል፡፡ የፖሊስ ቁልፍ ተግባርም ሃቀኛ፣ ሰው አክባሪ እና እምነት የሚጣልበት የደህንነት አካል በመሆኑ ነው፡፡

የተለያዩ የሥነ ምግባር ደንቦች የፖሊስ መኮንኖችን ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል፡፡ የሥነ ምግባር ደንብ እኛ እንዳሰፈርነው ሁሉ የፖሊስ ሰራተኞችም በሃቀኝነት ብቻም ሳይሆን “በሐቀኝነትም ሀቀኛ” ሆነው መገኘትንም ይጠይቃል፡፡  ሥነ ምግባር እና ታማኝነት ለፖሊስ አለቃ ወይም መኮንኖች አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የፖሊስ መኮንን የተቋቋመውን ህግ እና ደንብ በማክበር ረገድ አርአያ መሆን ስላለበት፡፡ ሠላም!

     
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም