የህጻናት የልብ ህሙማን ማዕከል ዲጂታል ካርድ አገልግሎት ተግባራዊ አደረገ

100
ጥቅምት 14 ቀን 2012 የኢትዮጵያ የህጻናት የልብ ህሙማን ማዕከል በሶፍትዌር የታገዘ የታካሚዎች ዲጂታል ካርድ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ። በማዕከሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ'ኢንቲግሬትድ ዲጂታል ሄልዝ ማኔጅመንት ሲስተም' ሶፍትዌር በይፋ ስራ የማስጀመር መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል። የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፈቃዱ እንደገለጹት ሶፍትዌሩን በማዕከሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ የቆየ ሲሆን የሙከራ ስራዎችም ተከናውነዋል። የሙከራ ስራዎቹም በካርድ መጥፋትን የሚደርሱ ችግሮችን የሚያስቀርና አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ በኩል የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት ያመላከተ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የገለጹት። ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ለ5 ሺህ 500 ህሙማን የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠቱንም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው ይህንን የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል በኩል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ በመሆኑ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል። የ'ኢንቲግሬትድ ዲጂታል ሄልዝ ማኔጅመንት ሲስተም' ሶፍትዌሩ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች መዘጋጀቱን ጠቁመው በዚህም  ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መጪን ለማዳን መቻሉን ገልጸዋል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሶፍትዌሩ ከአንድ አመት በላይ ተግባራዊ ተደርጎ ያለ ምንም ችግር ውጤታማ ስራ እየተከናወነበት መሆኑንም አክለዋል ። ሚኒስትሩ እንደገለጹት ሶፍትዌሩ ለጤና ተቋማት በነጻ የሚቀርብ ቢሆንም በተቋማት በኩል ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ተነሳሽነት ያለመኖር ችግሮች ተስተውሏል። በበርካታ ጤና ተቋማት የሚያጋጥመውን የካርድ መጥፋትና የታካሚዎችን እንግልት ቴክኖሎጂው የሚያስወግድ በመሆኑም ተቋማቱ ቴክኖሎጂው ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ሶፍትዌሩን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል። ሶፍትዌሩን ለጎረሮቤት አገራት ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም