ይደምቃል ገና !

125
በእንዳለ ደበላ /ሀዋሳ ኢዜአ/ በሰላም መስክ ለኖቤል ሽልማት 301 ዕጩዎች ተፋጥጠዋል ። የአየር ንብረት ተከራካሪዋ የ19 አመቷ አውሮፓዊት ታዳጊ ግሪታ ታንበርግ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዋነኛ ተፎካካሪ ነበረች ። ድሉ ግን ኢትዮጵያዊው ጀግና መዳፍ ስር ገባ ። ውጤቱ አለምን ያሰፈነደቀ ታላቅ ድል ሆኖ ተመዝግቧል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ዓመት ውስጥ ባከናወኑዋቸው አንፀባራቂ ተግባራት የሰላም ኖቤል ማሸነፋቸው ደግሞ  ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ፋይዳው የላቀ ነው ። ስዊድናዊው ኢንጅነር የኬሚስትሪ ባለሙያና ኢንዱስትሪያሊስት አልፍሬድ ኖቤል እ.አ.አ በ1895 ዓ.ም በኬሚስትሪ ፣ በስነጽሁፍ ፣ በሰላም ፣ በፊዚክስና በህክምናው መስክ የተለየ ተግባር ለፈፀሙ ግለሰቦች ሽልማት ለመስጠት የሚያስችል ተቋም መሰረተ። በኖቤል ስም የተመሰረተው ይህ አለም አቀፍ የሽልማት ተቋም መስራቹ አልፍሬድ ኖቤል በሞት ከተለየ ከዓመታት በኋላ በ1901   ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስቱ ዘርፎች ሽልማት መሰጠት ጀመረ። ለ68 ዓመታት በአምስቱ መስኮች ሽልማት ሲሰጥ የቆየው ተቋሙ በ1969 የምጣኔ ሀብት ዘርፍን በመጨመር ሽልማት የሚሰጥባቸውን መስኮች ወደ ስድስት ማሳደግ ቻለ። ተቋሙ እስከ ያዝነው 2019  ድረስ ለ800 ሰዎች በግልና በቡድን ባበረከቱት ደማቅ አስተዋፅኦ ልክ ሽልማት ሰጥቷል። ከነዚህ ተሸላሚዎች ውስጥ የዘንድሮውን ተሸላሚ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ሀያ አራቱ አፍሪካውያን ናቸው።ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ለአሸናፊነት የበቁት አገራቸውን ከተዘፈቀችበት አዘቅት ለማውጣት ባከናወኑት አኩሪ ተግባር ነው ። ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ፣ ለቁጥር የሚያዳግት የስራ አጥነት መስፋፋት ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖርና የድህነት መጠን መጨመር ፣ የኑሮውድነት መባባስ ፣ ከማስታገስ የዘለለ መፍትሔ የማያመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  የመሳሰሉት ችግሮች የህዝብ ቁጣ መቀስቀሳቸውን ተከትሎ ለውጥ ሊመጣ ግድ ይል ነበር ። በለውጡ ወደ መሪነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት ስራቸውን ጀመሩ ። በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ፈቱ ። በስደት ላይ የነበሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ አደረጉ ። የታግደው የነበሩ የመገናኛ ብዙሀንና ድረገፆችን በመክፈት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪክ ሰሩ፡፡ እርስ በእርስ በብሄርና በጎሳ ተከፋፍሎ በጎሪጥ ይተያዩ የነበሩ የሀገሪቱ ህዝቦችን አንድ ለማድረግ “ በፍቅርና መደመር” መርህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ማነሳሳት በመቻላቸው በየአካባቢው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፎች ተደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥ እያከናወኑ ካሉት መረጋጋትና ሰላም የማስፈን ስራ ጎን ለጎን በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለአመታት የቆየውን ቅራኔ ለመፍታት ያላቸውን አቋም ይፋ አደረጉ ። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የተጀመረው ውዝግብ ወደ ጦርነት አምርቶ በሺዎች ለሚቆጠሩ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ህይወት መጥፋት ፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ለሁለት አስርት ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ የቆዩትን ሀገራት ወደ ቀድሞው ፍቅራቸው በመመለስ ዓለምን ያስደነቀ ተግባር ፈፅመዋል ። በሀገራቱ መካከል ዕርቅ ለማውረድ ወደ አስመራ ስልክ በመደወል የመጀመሪያው የግንኙነት ምዕራፍ ከፈቱ ። ይህንኑ ተከትሎ በኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አንድ ብሎ የተጀመረው ግንኙነት ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አስመራ በማምራት እንዲጠናከር አደረጉት ። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሰላም ለማውረድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳየት መቻላቸው ደግሞ ሊጠገን አይችልም ተብሎ የነበረውንና ለሁለት አስርተ ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ወደ ሰላም መቀየሩ አለምን አስደመመ ። ይህን ሁኔታ ኬንያዊቷ የቢቢሲ ዘጋቢ ኤልዛቤት ኦሄን የአውሮፓውያኑ 2018 የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ በዓመቱ ታሪክ የሰሩ አፍሪካውያንን በማስመልከት አንድ ዘገባ አወጣች። በቢቢሲ ድረገጽ ላይ የኢትዮ-ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር “ፀሀይን ከምእራብ በኩል እንድትወጣ እንደማድረግ ነው” ስትል ባወጣችው ዘገባዋ የሁኔታውን አይታመንነት ገልጻ ነበር። የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰምሮ ድንበሮች ተከፍተው የአየር ትራንስፖትና የስልክ ግንኙነት መጀመራቸው ዓለምን አጀብ አሰኘ፡፡ ዓለምን ማስደነቅ አጠናክረው የቀጠሉት ጠቅላይ ሚስትር አብይ አህመድ የካቢኔያቸውን ግማሽ በሴቶች እንዲደራጅ በማድረግ አደመቁት ። ርዕሰ ብሄርነቱን ጨምሮ ቁልፍ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ለሴቶች በመስጠት ታሪክ መስራታቸውን በዘገባዋ ጠቁማ ነበር። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መልሰው ደጀኔ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርም ኩራት መሆን የቻለ ነው። ከዚህ ባለፈም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በግጭትና በቅራኔ ሲታመሱ የቆዩትን ደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ ፣ ሱዳን ፣ ኬንያ ፣ ጅቡቲና ኤርትራ የውስጥ ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የማቀራረብ ውጤታማ ስራ አከናወኑ ። ይህ ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ መሪነት በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዋነኛ አጀንዳ መሆን አስቻላቸው ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ። የዕምነት ተቋማት በውስጣቸው የነበረውን መከፋፈልና ልዩነት ለመፍታት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀትና በማወያየት ልዩነቶቻቸውን ፈትተው አንድ እንዲሆኑ ማድረግም ችለዋል ። ከሀገር ውጪ በተለያዩ አህጉራት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወደ ስፍራው በመጓዝ በማንኛውም መስክ ለሀገራቸው እንዲሰሩ ያቀረቡትን ጥሪ ድጋፍ አስገኘላቸው ። በተለያዩ ሀገራት እስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ መቶ ሸህ የሚጠጉ ዜጎችን ማስፈታትና ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ በማድረግም የራሳቸውን ታሪክ ይበልጥ አደመቁት ። እነዚህ ተግባራት ያስገኙላቸው ተቀባይነት በፎርቢስ መጽሄት በዓለማችን አስር ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ተርታ ስማቸው እንዲሰፍርና ለሰላም ኖቤል እጩ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑን ዶክተር መልሰው ይናገራሉ። ታዲያ! ይህን ተግባር ያከናወኑና አይሆንም ተብሎ የነበረውን የኢትዮኤርትራ ችግር በመፍታት ሰላም ማውረድ የቻሉ ሰው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆን የመጀመሪያው እንጂ ሌላም ሽልማት ይገባቸዋል ። በዚሁ የዩኒቨርሲቲ በውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ምህረትአብ አብርሀም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።“የመጀመሪያ የኖቤል ተሸላሚና ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው አስደሳች እንዲሆን ያደርገዋል እንጂ ስራቸው ከዛ በላይ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ። በ1951 ደቡብ አፍሪካዊው የህክምና ባለሙያ ማክስ ቴይለር በመስኩ ባበረከቱት ተግባር የመጀመሪያው አፍሪካዊ ኖቤል ተሸላሚ ሆነው ስማቸው በክብር መዝገብ ሰፍሯ ። በ1957 የአፍሪካ ደም ያላቸውን ትውልደ አልጄሪያዊ /በዜግነት ፈረንሳይ ናቸው/ አልበርት ካሙስን በስነጽሁፍ መስክ ሁለተኛው አፍሪካዊ ተሸላሚ ለመሆን በቁ። በ1960 በአፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊው አልበርት ሉቱሊ ሶስተኛው አፍሪካዊ ናቸው። በግብጽና በእስራኤል መካከል ያለውን ቅራኔ በመፍታት ሰላም እንዲወርድና ለእስራኤል ዕውቅና በመስጠት ባበረከቱት አስተዋጽኦ በወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ሜንካሀም ቤጊን ጋር የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ግብጻዊው አንዋር ሳዳት አራተኛው አፍሪካዊ ሎሬት ሆኖው ተመዝግበዋል ። በአጠቃላይ ከአፍሪካ ኖቤል ተሸላሚ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ በሰላም አራት፣ በህክምና ሶስት ፣ በስነጽሁፍ ሁለት እንዲሁም በኬሚስትሪ አንድ በአጠቃላይ 10 የኖቤል ሽልማቶችን አግኝታለች። ግብጽ በሰላም ሁለት፣ በስነ ጽሁፍ አንድ እንዲሁም በኬሚስትሪ አንድ በአጠቃላይ አራት ኖቤል በመውሰድ ከአፍሪካ ሁለተኛ ስትሆን ሁለት የሰላም ኖቤል ሽልማት በመውሰድ ላይቤሪያ ሶስተኛ ናት ። ናይጄሪያ በዎሌ ሶይንካ በስነጽሁፍ ፣ ጋና በኮፊ አናን፣ ኬንያ በዋንጋሪ ማታይ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዴኒስ ሙኩዌጌ እና ኢትዮጵያ በዶክተር አብይ አህመድ በሰላም አንዳንድ ኖቤል የወሰዱ 24 የአፍሪካ ሀገራት ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ 100ኛው በሰላም ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ በመሆን በክብር መዝገቡ ስማቸው የሰፈረ ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ የአውሮፓውያኑ 2019 ሊጠናቀቅ 21 ቀናት ሲቀሩት በኖርወይ ኦስሎ ከ900 ሺህ ዶላር በላይ ሽልማት ይቀበላሉ። ” የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ይታወቃል” ይባል የለ ?  ሰውየው ገና ብዙ ተአምር ይሰራል ። የበለጠም ይደምቃል ። ሽልማቱ ለእኛው የተሰጠ የእኛም  መሆኑን ተገንዝበን ለተሻለ አንፀባራቂ ስኬት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መቆም ከቻልን የድርብ ድርብርብ ድሎች መሆናችን አይቀርም ። አምና ኮንጓዊው ዶክተር ዴኒስ ሙኩዋጌና ናዲያ ሙራድ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት እንዲቆም በጋራ ባበረከቱት አስተዋጽ የሰላም ኖቤል ሽልማት መውሰዳቸው በማስታወስ ቸር እንሰንብት ብለን መሰነባበቱን መረጥን ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም