በህክምናው የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን ታካሚዎች ተናገሩ

44
አምቦ ጥቅምት12 /2012 የአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል ባመቻቸላቸው ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን ታካሚዎች ተናገሩ። በአገልግሎቱ ከፍለው መታከም የማይችሉ 250 የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ከተጠቃሚዎቹ መካከል በምዕራብ ሸዋ ዞን የዳኖ ወረዳ ነዋሪአቶ ወንድሙ ተሰማ አንዱ ሲሆኑ የአንድ ዓይናቸውን ብርሃን ካጡ አስር ዓመታት ያህል እንደሆናቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። ሁለተኛው ዓይናቸውም ለሶስት ዓመታት እይታው ቀንሶ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የሰውን እርዳታ እንዲጠይቁ አድርጎአቸዋል፡፡ ሆስፒታሉ ባመቻቸላቸው ነጻ ህክምና የሁለቱ ዓይናቸው ብርሃን መልሰው በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋልል። በዓይን ህመም ምክንያት ከልጅነታቸው ጀምሮ ህመም ሲሰማቸው መቆየቱንና ከሶሰተ ዓመት ወዲህ ሙሉ በሙሉ ማየት እንደተሳናቸው ተናገሩት ደግሞ የድሬ እንጪኒ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ምንትዋብ ገላልቻ ናቸው ፡፡ በሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ባለሙያዎች በተደረገላቸው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ዳግም ማየት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ “የዓይን ብርሃኔ ዳግም በመመለሱ ሠርቼ ቤተሰቤን ለማስተዳደር እንድችል በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል “ብለዋል ፡፡ የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ደፈርሻ ከበበው እንዳሉት የዓይን ብርሃኔ ማየት ያቆመው በ2010 ዓ.ም ነው። ”ወደ አምቦአጠቃላይ ሆስፒታል መጥቼ ዛሬ ህክምናውን ሳገኝ የአጣሁትን የአይን ብርሃን መልሼ ስላገኘሁ ተደስቻለሁ” ብለዋል። ታካሚዎቹ በተደረገላቸው ነፃ ህክምና ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል የዓይን ስፔሻሊስት ዶክተር ምህረት ደዬሳ እንደገለፁት ህክምናው የተሰጠው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍልና ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጄክት በተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት የገንዘብና የባለሙያ ትብብር ነው። ህክምናው ለሶስት ቀናት የተሰጠ ሲሆን ከምዕራብ ሸዋ ዞንአምቦ፣ጅባት፣ደንዲ፣ድሬ ኢንጪኒ፣ ቶኬ ኩታዬና ዳኖናነኖኖ ወረዳዎች የመጡና ከፍለው መታከም የማይችሉ 250 የህብረተሰብ ክፍሎችተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ የሂማሊያን ካታራክት ፕሮጄክት አስተባባሪ አቶ አሳሳኽኝ ንጉሴ” ከፍለው መታከም የማይችሉ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂዎችን ከዓይነ ስውርነት ለመታደግ ህክምናው ተሰጥቷል” ብለዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም