ሚኒስትሩ በኩታገጠም እርሻ ከ9 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች የተለያዩ የሰብል አይነቶችን ማምረት እንዲችሉ ማድረጉን አስታወቀ

40
ጥቅምት 12/2012 የግብርና ሚኒስቴር በኩታገጠም እርሻ ከዘጠኝ ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች የተለያዩ የሰብል አይነቶችን በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ዘመናዊ የምርት የምርት ማጨጃና መውቂያ መሳሪያ ባልደረሰባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ለማዳረስ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል። በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሩ በጋራ ተነጋግሮና ተደጋግፎ የሚሰራበት፣ በጋራ ገበያ ግብይት የሚፈጥርበት አሰራር በመሆኑ በበርካቶች ዘንድ መተግበር ጀምሯል። በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በ180 ወረዳዎች የተጀመረው የኩታ ገጠም እርሻ ሽፋን ወደ 430ወረዳዎች በማሳደግ በዘጠኝ ሰብል አይነቶች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። በኩታ ገጠም እርሻ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በመሸፈን በተያዘው የምርት ዘመን 9 ሚሊየን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት። የኩታገጠም ገበያ መር ሰብል ልማቱ በየዓመቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ በቀጣይም ችግሮችን በመፍታት የእርሻ ስርዓቱ ወዳልደረሰባቸው ከ400 በላይ ወረዳዎች ለማስፋት እየተሰራ ነው። የአትክልትና  ፍራፍሬ አመራረቱንም ወደዚሁ የአሰራር ስርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ከተወሰኑ ደረቅ አካባቢዎች ውጭ ጥሩ የዝናብ አገባብ፣ ምቹ የአየር ሁኔታ እንደነበር የገለጹት አቶ ኢሳያስ በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ የህብረት ስራ ማኅበራት ከቀረጥ ነጻ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖችን እንዲያስገቡ ያወጣውን ደንብ ለማስፈጸም ድጋፍ እያደረግን ነውም ነው ያሉት። የኮምባይነር ባለቤት የሆኑ ከ100 በላይ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ተቀናጅተው የሚሰሩበትን እድል ለማመቻቸት የጋራ መድረክ መደረጉን አውስተው፣ ምክክሩ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል። የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች በብዛት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች የተወሰኑትን ሌሎች ከፍተኛ ፍላጎት ወዳለባቸው አካባቢዎች የማዘዋወር ስራም ይከናወናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም