ኢትዮጵያና ሩሲያ በኒውክለር ቴክኖሎጂ አብረው ለመስራት ተስማሙ

110
ጥቅምት 12/2012 ኢትዮጵያና ሩሲያ በኒውክለር ቴክኖሎጂ አብረው መስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራረሙ። ስምምነቱ የተፈረመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ዛሬ በተወያዩበት ወቅት ነው። ሁለቱ መሪዎች በሶቺ ከተማ የሚካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ኢኮኖሚክ መድረክ ከተከፈተ ኋላ ሲሆን፤ ከድጋፍ ስምምነት በተጨማሪም የአገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይም መክረዋል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለፕሬዚዳት ፑቲን ስለኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሁኔታ አብራርተውላቸዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው "እንኳን ደስ አለዎ" በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። አገሮቹን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የሩሲያው የአቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ ናቸው። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የኒውክለር ሃይልን በጤናው ዘርፍ ለካንሰር ህክምና እና ለኃይል ልማት ለማዋል በምታደርገው ጥረት ላይ የሩሲያ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል። ድጋፉም በምርምር የልምድ ልውውጥ ማድረግን ያካተተ ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሩሲያ አፍሪካ መድረክ ከመሳተፍ ጎን ለጎን ግዙፍ ከሆኑ የሩሲያ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ያደርጋሉ። በዚህ መሰረት ማዳበሪያ በማምረት የካበተ ልምድ ካለው የአርላችም የተቀናጀ የኬሚካል ማምረቻና የማእድን ፍለጋ ላይ ከሚሰራው የጋዝፕሮም ዓለም አቀፍ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ። ሁለቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆኑ፤ በተለይ ጋዝፕሮም ዓለም አቀፍ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል በኃይድሮ ካርቦን ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ኩባንያው በኢትዮጵያ ወርቅ ፍለጋ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ መጠየቁም ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም