በሃዋሳ ከተማ የተፈጠረው ግጭት የሲዳማን ህዝብ ባህልና የጨምበላላን በዓል አይወክልም -የውይይቱ ተሳታፊዎች

5395

አዲስ አበባ  ሰኔ 12/2010 ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ የተፈጠረው ግጭት የሲዳማን ህዝብ ባህልና የጨምበላላን በዓል አከባበር አይወክልም ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በሀዋሳ ከተማ ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ይገኛሉ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት የሲዳማ ብሄር በባህሉ ከወላይታና ከሌሎች ብሄሮች ጋር ተመሳሳይ ባህልና የኑሮ ዘይቤ የሚጋራ፣ ባለፉት ዘመናትም በርካታ ክፉና ደጉን አብሮ ሲጋፈጥ እንደኖረ አንስተዋል።

የፍቼ ጫምበላላ እለትም “እንኳን የሰው ህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ ቀርቶ እንስሳት እንኳን የማይነኩበት ቀን እንደሆነ” ገልጸዋል።

ግጭቱ የዚያን ቀን መቀስቀሱ ተገቢ እንዳልሆነና ከባህላቸው ጋር የሚቃረን እንደሆነም አክለዋል ነዋሪዎቹ።

የሲዳማ ህዝብ ግን ጥያቄ እንዳለው ተሳታፊዎቹ ያነሱ ሲሆን ከጥያቄዎቹም መካከል ለ12 ዓመታት ሲንከባለል የቆየው ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም የክልል ጥያቄ፣ በሀዋሳና አካባቢው የሚሰሩ ትላልቅ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ በልማት ምክንያት የሚነሱ አርሶ አደሮች ተገቢውን የካሳ ክፍያ አለማግኘትና ለጎዳና ኑሮ መዳረግ፣ የወጣቶች ስራ አጥነትና ጎዳና ላይ ቆመው የሚውሉ ወጣቶች ቁጥር መብዛት በአሳሳቢነት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ሆኖም ግን ጥያቄዎቻቸውን በሰላም ማቅረብ እንጂ ከሌሎች ብሄሮች ጋር ግጭት ውስጥ  መግባት ተገቢ እንዳልሆነና እንደማይወክላቸው ነው ያስረዱት።

“የተፈጠረው ግጭትም ይሄንን የወጣቱንና የህዝቡን ጥያቄ ”ስስ ብልት” የሚያውቁ ሌላ ዓላማ ያነገቡ፤ ይህንን ተጠቅመው ህዝብ ለህዝብ ለማጋጨት ያደረጉት ጥረት ነው” ብለዋል።

ህዝቡ በሚሰበሰብበት እለት መርጠው ግጭት መቀስቀሳቸውም ሆነ ተብሎ የተሰራ ሴራ መሆኑንም ባላቸው ጥርጣሬ ገልጸዋል።

በቀጣይም መንግስት የዚህን ሴራ ጠንሳሾች አጣርቶ እንዲያሳውቃቸው ጠይቀዋል።

ከክልሉ ጥያቄ ጋር ተያይዞ በርካታ የብሄሩ ተወላጆችና ሙሁራን ለእስርና ለስደት እንደተዳረጉ በመግለጽ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

ህዝቡ የሚያነሷቸው ጥያቄዎቸ ቶሎ መልስ አለመስጠትና ሸፋፍኖ ማለፍ በአካባቢው የተለመደ መሆኑንም ገልጸው፤ ለዚህም ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሹም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሳው ጥያቄ ከደቂቃዎች በኃላ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።