ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስርዓት መሻሻል ለአገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት ያግዛል- ሰላም ሚኒስቴር

93
አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012  በኢትዮጵያ ወንጀልን የመከላከልና የመቆጣጠር ስርዓቱ መሻሻሉን የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ግብረ ኃይል እውቅና መስጠቱ የውጭ ንግድና የኢንቨስትመንት አቅሟን እንሚያሳድግላት የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ኢትዮጵያ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ በማስመሰል ማቅረብ እንዲሁም ሽብርተኝነትንና የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስርዓቷን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻለች መሆኗን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ግብረ ኃይል ሰሞኑን አሳውቋል። ይህንን ተከትሎም የሰላም ሚኒስቴር ይህንን የወንጀል መካላከልና መቆጣጠር ስራዋ መልካም ውጤት በማምጣቱ በአገሪቷ በተለይም የኢኮኖሚውን ዘርፍ በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመግለጫው አስታውቋል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በተለይም እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ በህገ ወጥ ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ በማስመሰልና ሽብርተኝነት መደገፍን የመቆጣጠርና የመከላከል እርምጃዋ በተለየ መልኩ ክትትል ሲደረግባት እንደነበር ያስታውሳሉ። በማንኛውም ወንጀል የሚገኘውምን ገንዘብ ህጋዊ በማስመሰል የሚከናወን እንቅስቃሴ የአገርን ኢኮኖሚ ከማዳከም ባለፈ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ እንደሚከትም ገልጸዋል። በመሆኑም አገሪቷ ይህንን ወንጀል የመቆጣጠርና የመከላከል አቅሟ ጥያቄ ውስጥ መግባቷ አገሪቷ ከውጭ አገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያዳክም ይሆናልም ብለዋል ሚኒስትሯ። ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ መንግስት በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ ስርዓትን በመዘርጋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴና ተግባራት ማሻሻሉን የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ግብረ ኃይል ሰሞኑን ባካሄደው ግምግማ አረጋግጦ የጥብቅ ክትትሉን ማዕቀብ እንዳነሳ ገልጸዋል። አገሪቷን ከህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በመከላከሉ ረገድ መንግስትም የቁጥጥሩን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ይህም በመሆኑ በተለይም ከአውሮፓ ህብረት አገራት ጋር የሚካሄደውን የግብይት ስርዓት የሚያሻሽልና የአገሪቷን መልካም ገጽታ በመገንባት የኢንቨስትመንትን ፍሰት እንዲጨምር ያስችላል ሲሉ ወይዘሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል። እንዲሁም በላኪዎችና አስመጪዎች በኩል ያለውን እንቅስቃሴም እንደሚደግፍና የባንክ አገልግሎት ትስስርን እንደሚያሳድግም ተናግረዋል ። የዚህ ዓይነቱ ወንጀልም በማንኛውም የወንጀል ድርጊት የሚገኘውንም ገንዘብ ህጋዊ ማስመሰል፣ ሙስናና ግብርን ማጭበርበርንም እንደሚያካትት የገለጹት ሚኒስትሯ በተለይም ከአገር ውስጥ የሸሹ ህብቶችን ለማስመለስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከውጭ አገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አንዲህ አይነት ወንጀልን ከምንጩ ለማድረቅም መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት። የፋይናንስ ወንጀል መካላከል ዳይሬክተር አቶ ኪዳነማሪያም ገብረጻዲቅ በበኩላቸው በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል በርካታ ስልቶችና ተግባራት እንዳሉ ይገልጻሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም