ውህደቱ ኢትዮጵያ አንድነቷንና ሰላሟን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደርጋታል- ምሁራን

66
ደሴ ጥቅምት 11 ቀን 2012 በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የሚጠበቀው ውህደት ኢትዮጵያ አንድነቷንና ሰላሟን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደርጋታል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ። ውህደቱ በውይይትና በመግባባት ሊከናወን እንደሚገባውም አሳስበዋል። ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳስረዱት ኢህአዴግ ራሱን አንድ ፓርቲ ለማድረግ የሚያደርገው ውህደት አገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያስችላል ብለው ያምናሉ። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ-ጹሁፍ መምህርና የግጭት አፈታት ተመራማሪ ዶክተር ገብረየሱስ ተክሉ ውህደቱ ለኢትዮጰያ አንድነት ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱትን የጸጥታ ችግሮ በዘላቂነት ለመፍታትና አንድነትን ለማስጠበቅም ውህደቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአገር መሪ ለመሆን ሳይችሉ የቀሩ  አጋር የተባሉ ክልሎች አመራሮች  በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩና ሕዝባቸውንና አገራቸውን በመልካም መንፈስ እንዲያገለግሉም ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ተዋህዶ አንድ ካልሆነ እየተስተዋለ ያለው መተቻቸት፣ መናናቅና የጸጥታ ችግር እየተባባሰ እንጂ፤እየቀነሰ አይሄድም ሲሉም ግምታቸወን አስቀምጠዋል። ውህደቱ አሁን ባለው የፖለቲካ ጡዘትና ፍጥጫ ሳይሆን፣ በየደረጃው ውይይትና መተማመን ተፈጥሮ  ሊከናወን እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ በበኩላቸው ውህደቱ አግላይነትን ከማስወገድም ባለፈ፤ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና የመቻቻል እሴቶች ያጎለብታል ይላሉ፡፡ በሕዝብ ተጋድሎ የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስም መሪው ድርጅት ጥቅሙ ያልገባቸውን ማስረዳት፣ ማወያየትና ማደራደር ይገባዋል ባይ ናቸው። በአገሪቱ ያሉት ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተዋህደው በሚኖሩባት አገር ''ውህደቱ ጨፍላቂና አሃዳዊ ነው'' የሚባለው  አመለካከት ግን መሠረተ ቢስና ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው ከንቱ ቅዠት ነው ብለዋል፡፡ አተገባበሩ ጥንቃቄ ለሚፈልገው ለዚህ ውህደት አባልም ሆኑ አጋር ድርጅቶች ለሕዝቡ የሚበጀውን ማስቀደም እንዳለባቸው ያሳሰቡት ምሁር፣እርስ በእርስ ከመጠላላት ተቆጥበው አንድ መሆን መቀጠል ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ጥቅመኞች ኅብረተሰቡን በብሄርና በሃይማኖት ከፋፍለው አገርን በማተራመስ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት በሚሮጡበት በዚህ ወቅት ውህደቱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ ጽሁፍ መምህርና የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ተሾመ መንገሻ ናቸው፡፡ ውህደቱ አገራዊ መግባባትን የሚፈጥርና አዲስ የፖለቲካ ህዳሴ ነው ያሉት ምሁር፣ ውህደቱ ወደ ትግበራ ሊገባ ሲል ማፈግፈግ ለኢትዮጵያ አይመጥንም ብለዋል። በአንዳንድ ድርጅቶች ውህደቱን እንደ ጭፍለቃና አሃዳዊ  ሥርዓት መመለስ አድርጎ  ማቅረብም  ነው ተገቢ አይደለም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም