ለምርጫው ስኬታማነት ህዝቡ የበኩሉን አስተዋኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

65
ኢዜአ ጥቅምት 11/2012 ዘንድሮ የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የበኩሉን አስተዋኦ እንዲያበረክት ተጠየቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዘንድሮ ምርጫ ማካሄድ የግድ በመሆኑ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ይሁንታን ያገኙ ሰዎችን በመመደብ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቦርዱ አወቃቀርና የምርጫ ህጉን በማሻሻል፣ በቂ በጀት በመመደብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማሟላት ከዚህ በፊት ከተደረጉት ምርጫዎች የተሻለ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ብርሃኑ መኩዬ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርጫው በተቀመጠው ህግና ስርዓት ተፈጻሚ እንዲሆን ህዝቡ ድጋፍ ማድረግ አለበት። ''ለምርጫው ውጤታማነት ሁሉም አካል ዝግጁ ሆኖ ከተንቀሳቀሰ በየትኛውም ቦታ ችግር ሊገጥም አይችልም'' ብለዋል። እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ ምርጫው ከችግር የጸዳ ባይሆን እንኳ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት፣ በህግና በስርዓት እየፈቱ ትክክለኛውን አቅጣጫ መከተል ይቻላል። ምርጫው በፓርቲዎችና በግለሰቦች መካከል የሚደረግ ውድድር በመሆኑ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም እንደ ዜጋ እና እንደ ህዝብ ተመራጭ አካል ለምርጫው ስኬታማነት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕቅዱ መሰረት የሚያከናውናቸው ተግባራት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየሄደ መሆኑን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የሚጠበቅ ግዴታ እንደሆነም ገልጸዋል። እንዲሁም መራጮች ለሰላማዊ፣ ለዴሞክራሲያዊና የህዝብ ተሳትፎ ለተረጋገጠበት ምርጫ እንዲዘጋጁ የምክር ቤቱ አባላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸውም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል። ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ታደሰ ኦርዶፋ በበኩላቸው ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች በሰከነ ሁኔታ እንዲቀሳቀሱ ፓርቲዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ''በአንዳንድ አካባቢዎች በሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የምርጫ ጊዜን ማሻገር ሳይሆን ችግሮቹን ለማስወገድ መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝቡ ጋር ሊሰሩ ይገባል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በርካታ አባላት ያሉት ፓርቲ እና ገዢ መንግስት በመሆኑ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብዙ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም አቶ ታደሰ አስረድተዋል። እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከዚህ በፊት በተመረጡባቸው አካባቢዎች ካሉ የአስተዳደር አካላት ጋር በመተባበር ለምርጫው ስኬታማነት በትብብር በመስራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ገልጸዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም