መረጃና አዋጁ

131
ሚስባህ አወል /ኢዜአ/ አዲስ አበባችን የእግረኛ መንገዶቿን በተዋቡ  የሸክላ ጡቦች ማሰዋብ ጀምራለች፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ትኩረቶች ሁሉ ለሰብአዊው ሳይሆን ለቁሳዊው የመኪና “ጎማ” ብቻ እንደነበር እግረኞች በሚገባ ያውቁታል፡፡ አሁን በመዲናዋ የሚስተዋለው የእግረኛ መንገዶችን የማስዋቡ ስራ ለግዑዙ ጎማ ብቻ ሳይሆን ለሰብዓዊ ፍጡሩም ትኩረት እየተቸረው ለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው፡፡ በተለይ በክረምቱ ጊዜ ጎርፉ የእግረኛ መንገዶችን ብቻ ሳይሆን አስፓልቱንም ስለሚሞላው ቅንጡ ጫማዎችን ተጫምቶ ብትን ማለት አይታሰብም፡፡ ጫማቸውን አውልቀው በባዶ እግራቸው ጎርፉን ለማቋረጥ አሊያም ደግሞ በደንጋይና በብሎኬት መዛለያ ለሚያዘጋጁ ወጣቶች ብር እየከፈሉ መሻገር ግድ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ሲብስ ደግሞ ወጣቶች ገንዘብ እያስከፈሉ እግረኛውን በጀርባቸው እንደ ህጻን ልጅ አሽሩሩ እያሉም ያሻግራሉ፡፡ የመዲናችን እግረኛ መንገድ  የዛሬ ርዕሰ ጉዳዬ ማጠንጠኛ ባይሆንም  ለአዳማው የእግረኛ መንገድ እንደ መነሻ ይሆነኝ ዘንድ ነው ሃሳቡን ማንሳቴ፡፡ አዳማ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ የሀገራችን ከተሞች መካከል ነች፡፡ ይህን ደግሞ በቅርቡ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው ስልጠና ላይ ለመሳተፍ አዳማን እግሬ በረገጠበት ወቅት በአይኔ አይቼ ተገንዝቤዋለሁ፡ አዳማን ብዙ አላውቃትም፡፡ ከአስር ዓመት በፊት እንዲሁ ገባ ብዬ ወጥቸባታለሁ፡፡ የተሳፈርኩበት ሚኒባስ በአዲሱ አዲስ-አዳማ የፍትነት መንገድ  ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አክለፍልፎ ከአዳማ መግቢያ አካባቢ ነበር ዱብ ያደረገኝ፡፡ ከፍ ባለው ቦታ ከፍ ያለ ግርማ ሞገስ ተጎናጽፎ ከተማዋን ቁልቁል የሚመለከተውን የሰማዕታት ሃውልት በአግራሞት እየተመለከትኩ በእግሬ ወደ መሃል ከተማዋ ዘለቅኩ፡፡ የከተማዋ ታክሲዎች በአስፋልቱ ዳር በጥርብ ድንጋይ የተሰራውን መንገድ ተሳፋሪዎችን ይጭኑበታል ፤ ያወርዱበታልም፡፡ የእግረኛ መንገድነቱ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የእግረኛ መንገዱ ከአስፋልቱ ጋር ተመሳስሎ መሰራቱ ታክሲዎቹ እንደልባቸው እየዘለሉ እንዲገቡበት በር ከፍቶላቸዋል፡፡ግራ ቢገባኝ ቆም ብዬ ጉዳዩን ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ የአዳማ አስፋልት መንገዶች ጠባብ በመሆናቸው ታክሲዎቹ አስፓልቱ ዳር ላይ ቆመው ሰው ለማሳፈር ቢሞክሩ ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡ በርግጥ ለሁለት የተከፈለው አስፋልት ለከተማዋ ድምቀትና ውበት ቢያጎናጽፋትም  ጥበቱና በአስፋልቱ ዳር የሚከናወኑ ግንባታዎች ወደፊትም ቢሆን መንገዶቿን ለማስፋት ትልቅ እንቅፋት ሊሆኑባት እንደሚችሉ ለመገመት የመምህንድስና አዋቂ መሆንን የግድ የሚል አይመስለኝም፡፡ ወበቃማውን የአዳማ አየር ለስለስ ለማድረግ የሚነፍሰውን አየር እየማግኩ ግራና ቀኝ የተገነቡትንና በመገንባት ላይ ያሉትን ህንጻዎች በአርምሞ እየቃኘሁ ጉዞዬን ቀጥያለሁ፡፡ አብዛኞቹ ህንጻዎች ሆቴሎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከተማዋ ከመዲናዋ በቅርብ ርቀት ላይ እንደመገኘቷ መጠን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እየሆነች የመጣች ከተማ ለመሆኗ ማረጋገጫ ነው፡፡ በአዳማ ጠዋት ጠዋት ከመላ ሀገሪቱ የመጡ የኮንፍረንስ ተሳታፊዎችን  ውር ውር ሲሉ ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል፡፡ እኔስ አንዱ ተሳታፊ አይደለሁ! ከመሃል “ፍራንኮ ሰፈር አውራ ጎዳና” በሚለው ታክሲ ተሳፍሬ  ወደ “ደብሊው” የስልጠና ማዕከል ተጓዝኩ፡፡ በዚህ የስልጠና ማዕከል 50 የሚጠጉ የህዝብና ግል መገናኛ ብዙኃን  ባለሙያዎች በስልጠናዉ ለመካፈል  በቦታው ተገኝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ  አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለህዝብ የሚያደርጉት ተጠባቂ ንግግር ሲጀመር  አዳራሹን ለቀን ቴሌቪዥን ወደሚገኝበት ካፍቴሪያ ተሯሯጥን፡፡ ንግግሩ እንዳለቀ ስልጠናው ተጀመረ፡፡ ስልጠናው በመገናኛ ብዙኃን ነጻነት አዋጅ፣ በሰላምና ልማታዊ ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከመረጃ ነጻነት አዋጁ ጋር በተያያዘ የተሰጠው ስልጠና ሳቢና የመድረክ ላይ ውበትን የተላበሰ ቢሆንም በአዋጁና መሬት ላይ ባለው አተገባበር መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ግን ሰልጣኞችን ሳያስደመምማቸው አልቀረም፡፡ ይህን ስልጠና የሰጡን በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል መምህር የሆኑት ዶክተር ጌታሁን ካሳ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳነሱትም በአብዛኛው በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ህግጋት ተፈጻሚ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ በተለይ ደግሞ ገደብ የተጣለባቸው መረጃዎች በድፍኑ የተቀመጡ በመሆናቸውና የተሟላ  ማብራሪያ ያላካተቱ መሆናቸው ጋዜጠኛው በፈለገውና በተቻለ ፍጥነት መረጃ እንዳያገኝ አድርገውታልም ነው የሚሉት፡፡ አብዛኛው ጋዜጠኛ በሃሳባቸው ስለመስማማቱ ከድባቡ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በመድረኩ ላይ ጋዜጠኛው ገደብ ያልተደረገበትንም መረጃ ለማግኘት በሚንቀሳቀስበት ወቅት ተፈላጊውን መረጃ መስጠት ያለባቸው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደ ስብሰባና የመስክ ስራ በመሳሰሉ ምክንያቶች ከህዝብ ሲሸሹ የሚከሰሱበትንና የሚወቀሱበትን ሁኔታ አዋጁ በአግባቡ አለማካተቱንም ጋዜጠኞች በምሬት ጭምር ሲያነሱ ሰምቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 ካሰፈራቸው አንቀጾች ውስጥ 11ኛው አንቀጽ ተነጻጻሪ የህዝብና የግለሰብ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የወጡ ተገቢ ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው  ከማንኛውም መንግስታዊ አካል ዜጎች መረጃን ለመጠየቅ ፣ ለማግኘት እና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብት ተፈፃሚ ስለማድረግ ይደነግጋል፡፡ አዋጁ በተለያዩ ተልካሻ ምክንያቶችና ሰበባሰበቦች ሲሸራረፍ ቆንጠጥ የሚያደርግ አሰራር የለውም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው  እንደ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ሰብኣዊ መብትና የመንግስት ኮምዩኒኬሽን  ጽህፈት ቤት ያሉ መስሪያ ቤቶችም ቢሆኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ  አዋጁን ሊተረጉም የሚችል ደንብና መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ከሚል  የተለመደ ምላሽ የዘለለ መፍትሄ ሲሰጡ አይታይም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ  በውስጤ የሚመላለሱትን ጥያቄዎች ይዤ ወደ ስልጠናው ተሳታፊዎች አመራሁ፡፡ የታሪክሰው ታደሰ ይባባል፡፡ የናሁ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው ጋዜጠኛው መረጃን በፍጥነትና በጥራት አገኘ ማለት ህዝብ መረጃ አገኘ ማለት ነው፡፡ መረጃን በወቅቱ አግኘቶ ለህዝብ ጆሮ ማድረሱ  በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብን ለመፍጠር ለሚደረገው ሩጫ አጋዥ መሆኑ አያጠያቅምና ነው ጋዜጠኛው ይሕን ማለቱ፡፡ ይሁን እንጂ ወቅታዊ መረጃዎችን በሰዓቱ ወደ ህዝብ ለማድረስ ጋዜጠኛው ያለበት ፈተና ቀላል የሚባል እንዳልሆነም ነው ወጣቱ ጋዜጠኛ ያብራራልኝ፡፡ የታሪክሰው እንዳለው  መረጃ በችሮታ የሚሰጥ መሆን የለበትም፤ በህግና በደንብ ብቻ በመታጠር መረጃን ለማግኘት መሞከሩም ጥቅም የለውም፡፡ መመሪያ፣ ደንብና አዋጅ ብቻ  የሚፈለገውን መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡  የህብረተሰቡንም ሆነ የመረጃ ሰጪውን ግንዛቤ  የማሳደጉ ነገር ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡ መረጃን ያለአንዳች ቢሮክራሲያዊ አሰራር የመስጠት ልምድ ሊዳብር እንደሚገባም ነው ያብራራው፡፡ ሌላኛው የአዲስ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሙሉወርቅ ታፈረ ላነሳሁለት ጥያቄ ምላሹን የጀመረው “ይገርምሃል ከአንድ መንግስታዊ መስሪያ ቤት አንድ መረጃ ለማግኘት ስድስት ወር እንደወሰደብኝ ብገልፅልህ ታምነኛለህ?” በማለት ነበር፡፡ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን መረጃ በሰዓቱ ማግኘት ሲሳነው “ወደማህበራዊ ሚዲያው ሄዶ  በተዛባ መረጃ ያልሆነ ነገር ውስጥ ቢገባ ይደንቀን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ሰንዝሮልኝ ወደ ስልጠናችን ተመለስን፡፡ በሞቀ ክርክር ታጅቦ የዕለቱ መርሃ ግብር እንደተጠናቀቀ አዳማን ግራና ቀኝ እየቃኘኋት ወደ አራዳ አቀናሁ፡፡ በአጋጣሚም  በተንጣለለ ግቢ ውስጥ የተገነባውን   የአዳማ ከተማ አስተዳደር አሻግሬ ተመለከትኩት፡፡ የአዳማ ከተማ የአስፋልትና እግረኛ መንገዶች ችግር ውስጤን ከንክኖታልና በአስተዳደሩ ስር ወደሚገኘው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ክፍል ጎራ አልኩ፡፡ የመጣሁበትን ጉዳይም ይመለከተዋል ለተባለው ባለሙያ አስረዳሁ፡፡ ባለሙያው ተፈላጊው መረጃ እጁ ላይ እንዳለ ሲገልጽልኝ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ባልተለመደ መልኩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰጠኝ አወንታዊ ምላሽ ምን አልባት በስልጠናው አብሮኝ የተሳተፈ ይሆን እንዴ? ስል ራሴን እስከመጠየቅም  አስገድዶኝ ነበር፡፡ ባለሙያው ብዙም ሳይቆይ “መረጃውን የምሰጥህ ግን ከመጣህበት መስሪያ ቤት ደብዳቤ አስጽፈህ በቅርብ ኃላፊዬ በኩል ወደ እኔ ከተመራልኝ ብቻ ነው” የሚል አጥር አስቀመጠልኝ፡፡ በስልጠናው ብዙ የተባለለትን አዋጅ ጠቅሼ በማባበልም በመማጸንም መረጃውን ለማግኘት ብዙ ጣርኩ፡፡ባለሙያው በአራዳኛ ቋንቋ “መስሚያ የለኝም!” በሚል መልኩ የአለቃውን ወንበር እያመላከተ ለምጠይቀው ጥያቄ ሁሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጠበ፡፡ እኔም ሙከራዬ ከንቱ መሆኑን ስረዳ ተነስቼ ወጣሁ!! ተስፋ አልቆረጥኩም ወደ ከተማዋ መሰረተልማት አቢይ የስራ ሂደት አስተባባሪው ተጠግቼ የምፈልገውን መረጃ ባለሙያው እንዲሰጠኝ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉልኝ ተማጸንኳቸው፡፡ እርሳቸውም ፈገግ ብለው “እኛ ባለን አሰራር ለሚዲያም ሆነ ለማንኛውም አካል ያለደብዳቤ መረጃ እንሰጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተውኝ  ቢሮውን ለቀው ወጡ፡፡ መረጃና የነፃነት አዋጁ ላይገናኙ ነገር  ስልጠና ገለመሌ ለምን እንደሚያስፈልግ እያሰላሰልኩ በከተማዋ ዘወር ዘወር ማለቴን ቀጠልኩ፡፡ የስራ ኃላፊዎቿ መረጃ ለመስጠት ደብዳቤ ቢጠይቁኝም አዳማ በአዲሱ አወቃቀሯ በስድስት ክፍለ ከተሞች መከፋፈሏን ወደ አራዳ መዞሪያ አደባባዩ ላይ ከተሰቀለው ባነር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ “ደብዳቤ”  “ስብሰባ” “መስክ”… የማትለዋን አዳማ ከእግር ጥፍሯ እስከ እራስ ጸጉሯ የማየት ጉጉቱ ቢያድርብኝም ያለኝ ጊዜ አጭር ነበርና  ተሰናብቻት ወጣሁ፡፡ በአዲሱ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ እኔና ነፍሰ-ስጋዬ እየተጨናነቅን አሁንም ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጉዘን ሳይሆን በረን አዲስ ከተምን!! በማግስቱ ከላይ በጋዜጠኞች የተነሱትን ቅሬታዎች ይዤ የፌደራል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተገኘሁ፡፡ ከውጭ የገቡ ጋዜጠኞች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ክልሎች ትብብር እንዲያደርጉ ደብዳቤ በመስጠት ስራ የተጠመዱት የጽህፈት ቤቱ የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ዳሬክተር ጄነራል አቶ መሀመድ ሰኢድ ከአንድ ሁለት ደቂቃ በሁዋላ አስተናገዱኝ፡፡ የመጀመሪያ ጥያቄዬ ከአዋጁ አስገዳጅነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አቶ መሀመድም ለአዋጁ የተዘጋጁ መመሪያና ደንቦች እስኪፀድቁ እንጂ አስገዳጅና ቅጣት የሚያስከትል አዋጅ መሆኑን አብራሩልኝ፡፡ እስከዚያው ግን ጋዜጠኛው የያዘውን መሳሪያ ተጠቅሞ መረጃ የማይሰጡ የተቋም ሀላፊዎችንም ሆነ የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎችን ለህዝብ በማጋለጥ የበከሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ነው የነገሩኝ፡፡ ጉዳዩ የህዝብ እንደመሆኑ በሁሉም ተሳትፎና በባለድርሻ አካላት ጭምር የሚከወን እንጂ ለአንድና ሁለት ተቋማት ብቻ የሚተው አለመሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡ ሰላም ሁኑ !!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም