በምዕራብ ሸዋ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 123 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ

59
አምቦ 11/2012  በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፈው የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ወደ መሰናዶ ትምህርት ላለፉና  ወደ ዩኒቨርስቲ ለገቡ 123 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ። ሽልማቱን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ያዘጋጁት የአምቦ ቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው፡፡ የማበረታቻ ሽልማቱ የተሰጠው በዞኑ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ውሰጥ የአስረኛ  ክፍል  ብሔራዊ  መልቀቂያ ፈተና አራት ነጥብ እና ከ271 በላይ ነጥብ ያመጡ 12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ናቸው፡፡ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ዳባ  በሽልማቱ  አሰጣጥ ስነስርዓት ወቅት አንዳሉት ሽልማቱ ታታሪ ተማሪዎችን በማበረታታት ሌሎችም የእነሱን ፈለግ ተከትለው ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ ለማነሳሳት ነው፡፡ ለተማሪዎቹ በነፍስ ወከፍ ላፕቶፕ ኮምፒተሮች ፣የማጣቀሻ መጽሸትና  የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከተሸላሚዎቹ መካከል 45 ተማሪዎች ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ኤ በማምጣት ከፍተኛ  ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣   ፣መምህራንና ፣ሱፐር  ቫይዘሮች፣ ርዕሰነ መምህራን ወላጆች ሽልማትና የምስክር ወረቀት  ተሰጥቷል፡፡ ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ያበቁ ትምህርት ቤቶችና የወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤቶችም የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከተሸላሚ ተማሪዎቹ መካከል ከአምቦ ሊበን መጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አራት ነጥብ ያመጣችው ተማሪ ፌኔቲ ተስፋዬ በሰጠችው አስተያየት ሽልማቱ ለበለጠ ውጤት  እንደሚያተጋት  ተናግራለች። ከግንደበረት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ታምራት ደጀኔ ሽልማቱ በመሰናዶ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት እንደሚያበረታታው ገልጿል፡፡ ለተሸላሚዎች ሽልማትና የምስክር ወረቀት የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ገላና ገብረሚካኤል እና  የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑረሳ ከሌሎች ሌሎችም የሥራ  ኃላፊዎች ጋር በመሆን ነው፡፡ ዶክተር ገላና ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት " ተማሪዎች ስኬታማ እንድትሆኑ ከማይረባ ድርጊት ተቆጥባችሁ ለትምህርታችሁ ትኩረት ስጡ" ሲሉ መክረዋል፡፡ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑረሳ ሽልማቱ ለዘጋጁት አካላት አመስግነው ተማሪዎች ለተሻለ ውጤት ጠንክረው እንዲሰሩ አበረታተዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም