በአገረቱ ካሉት ርዕሳነ መምህራን አንድ አራተኛውን ሴቶች ለማድረግ እየተሰራ ነው

75
ወልድያ ጥቅምት 11 / 2012  በአገር አቀፍ ደረጃ 10ሺህ ሴት መምህራንን ርዕሳነ መምህራን ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን የትምሀርት ሚኒስትሩ አስታወቁ። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ በወልድያ ከተማ ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት ለሴት መምህራኑ ሥልጠና የሚሰጠው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የተያዘውን ግብ ለማሳካት ነው። በዚህም ሴቶች የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በዕውቀትና በክህሎታቸው ልቀው የተገኙ መምህራን ተጨማሪ ስልጠና እንዲወስዱ በመሰራት ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ አገሪቱ ከ12 ዓመታት በኋላ የምትደርስበትን ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል። በፍኖተ ካርታው መሠረት ትምህርት በሦስት ምድቦች ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከ1ኛ-6ኛ ክፍል ያለው የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል መካከለኛ ደረጃ ተብሎ ይሰጣል። እንዲሁም ከዘጠነኛ-12ኛ ክፍሎች የሚሰጠው ትምህርት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ የሚል ስያሜ እንደሚኖረው ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በአገሪቱ 40ሺህ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም