በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመድሃኒት ጎጂ ባህሪያት መከታተያ ማዕከል ተከፈተ

53
ጥቅምት 11 / 2012 ዓም የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድሃኒት ጎጂ ባህሪያትን መከታተል የሚያስችል ማዕከል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፈተ። የመድሃኒት ጎጂ ባህሪያት ክትትል /ፋርማኮቪጅላንስ/ ስርዓት ለህመም መፈወሻ ተብለው የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ጎጂ ባህሪያት በሳይንሳዊ መንገድ ማወቅ የሚያስችል ነው። መድሃኒቶች በአመራረት፣ በአቀማመጥ፣ በአስተሻሸግ፣ በሃኪም ትዕዛዝና በሌሎች ለመድሃኒት ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች መጓደል ከፈዋሽነታቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተከፈተው ማዕከል ህሙማን በሚወስዷቸው መድሃኒቶች ላይ የሚታዩ የተለዩ ባህሪያትን በተዘረጋው ዘመናዊ አሰራር አማካኝነት ለምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ማሳወቅ የሚያስችል ነው። የጤና ባለሙያዎች ለማዕከሉ የተሰጠው የተጠቃሚ ስምና የይለፍ ቃል በመጠቀም በመድሃኒቱ ላይ የታዩ ችግሮችን መረጃ በማጠናቀር ለባለስልጣኑ ያሳውቃሉ። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳሬክተር ዶክተር ኬረዲን ረዲ እንዳሉት ባለስልጣኑ በሚያገኘው መረጃ መሰረት በመድሃኒቱ ላይ የታየው ችግር የተፈጠረበትን ምክንያት በላቦራቶሪ በማጣራት ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ እርምጃ ይወሰዳል። ከመድሃኒት ጎጂ ባህሪያት ጋር በተገናኘ በሚወለዱ ህጻናት ላይ የአካል ጉዳት፣ መድሃኒቱን የወሰዱ ህሙማንን ህይወት እስከማጣት የሚያደርስ ጉዳት እንደሚደርስ ተነግሯል። የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በዓመት 20 ሺህ መድሃኒትን የተመለከቱ ሪፖርቶች መደረግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። እንደ ዶክተር ኬረዲን ገለጻ በኢትዮጵያ በጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ እጥረት፣ በጤና ተቋማት ትኩረት አለመስጠትና መረጃውን ለማድረስ የተሟላ መሰረ ልማት ባለመኖሩ የሚቀርቡ ሪፖርቶች በዓመት ከአንድ ሺህ በታች ናቸው። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከተከፈተው በተጨማሪ በመቀሌ፣ በጅማ፣ በሃዋሳ፣ በባህር ዳርና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች ውስጥም ማዕከላቱ በዚህ ወር እንደሚከፈቱ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት የማዕከሉ በዩኒቨርሲቲ መከፈት የህክምና ሙያን የሚያጠኑ ባለሙያዎች በመድሃኒት ጎጂ ባህሪያት ላይ ተጨማሪ ምርምሮችን እንዲያድረጉ ያግዛል ብለዋል። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቀን ከሚያስተናግዳቸው አምስት ሺህ ከሚደርሱ ህሙማን ከመድሃኒት ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለባለስልጣኑ እንደሚያሳውቅም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ መድሃኒቶችን ከመውሰድ በመቆጠብ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እገዛ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል። የጤና ባለሙያዎችም ባለስልጣኑ በዘረጋው ነጻ የስልክ መስመር 8482 አማካኝነት ማሳወቅ ይችላሉ ተብሏል። ተቋሙ እስካሁን 34 እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን በ2011 ዓ.ም በጤና ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ የተረጋገጡ ሶስት መድሃኒቶች ላይ እርምጃ ወስዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም