የውህደት ጉዞው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መሬት ለማስያዝ ጠቀሜታው የጎላ ነው - የምክር ቤት አባላት

60
ጥቅምት 11 / 2012 ዓም የፓርቲዎች የውህደት ጉዞ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን መሰረት ለማስያዝ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋር ፓርቲዎቹ የውህደት ጉዞ ጀምረዋል። ጉዳዩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ሃሳቦች እየተሰነዘሩበት ቢሆንም ኢህአዴግ በሊቀ-መንበሩ በኩል ውህደቱ በጥናት የተደገፍና ውይይት ሲደረግበት የቆየ መሆኑን አሳውቋል። በዚሁ መሰረት ግንባሩ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማይተናኮል መልኩ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት እንደሚቀየር ታምኖበታል። አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና አባላቱም የዚሁ ፓርቲ አባል የነበሩና ተፎካክረው በስራ ላይ የሚገኙ ናቸው። ከምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ታደሰ ሆርዶፋ እንደሚሉት የፓርቲው አካሔድ የአግላይነት ባህሪ የነበረው በመሆኑ የውህደት ጉዳይ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት ውህደቱ ኢትዮጵያን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተሻለ መልኩ ለመምራት ትልቅ ዕድል ይዞ ይመጣል። በተለይም የፓርቲው አንድ መሆን ጠንካራ የፌዴራሊዝም ስርዓትን በመዘርጋት የክልሎች ራስን የማስተዳደር መብት እንዲጎለብት ያደርገዋል ብለዋል። አቶ ታደሰ የውህደቱ ጉዳይ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ሁሉም አውቆት ለስኬቱ ሊተባበር ይገባል ነው ያሉት። ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ደግሞ ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የቆየ ነው ብለዋል። የግንባሩ አካሄድ አጋር ፓርቲዎች ያሉባቸው ክልሎች ከዋና ዋና የአገሪቷ ውሳኔዎች ተገልለው እንዲቆዩ አድርጓል ይላሉ። በመሆኑም ውህደቱ ከዚህ በፊት በአገር ደረጃ የታሰበውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ውህደቱን የተመለከተ ውይይት አሁንም እስከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ ውይይት ቢደረግበት የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል። አቶ ዓለሙ ገብሬም እንዲሁ ውህደቱ በየትኛውም መልኩ መጨፍለቅ እንዳልሆነ ታውቆ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ። የፓርቲው ሁኔታ እስካሁን በግንባርነት ተሞክሮ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ቁርሾና አለመግባባቶች በስፋት እንዲስታዋሉ አድርጓል ነው የሚሉት። ውህደቱ እስካሁን የታዩ ችግሮን ከመቅረፍ ባሻገር ዜጎች አገራዊ አስተሳሰብ ኖሯቸው የተሻለ አገር እንዲገነቡ ያግዛል ብለዋል። በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ጊዜ ተወስዶ ውይይት የተደረገበት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ዓለሙ ዲንቃ ናቸው። ፓርቲዎች ሲዋሃዱ ጉልበት፣ኃይልና ጥንካሬ አግኝተው በከፍተኛ ሁኔታ ለአገራዊ ጥቅም እንዲሰሩ ሁኔታዎች ያመቻቻል ነው ያሉት። አቶ ዓለሙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ውህደቱ የተሻለ አገር ለመገንባት ጠቃሚ መሆኑን ተረድተው ሊያግዙ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም