በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት ይከበራል

95
ጥቅምት 11 / 2012 ዓም በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባሚ ተቋም አስታወቀ። 'ያልተሸራረፈ መብት ለሁሉም'' በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ቀኑ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያለውን የህብረተሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ዓላማና አሰራር ለማስተዋወቅ ያግዛል ተብሏል። የፊታችን ሀሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓም የሚከበረውን የመልካም አስተዳደር ቀን አስመልክቶ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር እንዳለ በዚሁ መግለጫቸው እንዳሉት በዓሉ፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ያለባቸውን ኃላፊነትና ተጠያቂነት በግልጽ በማሳየት ተባባሪ የሚሆኑበትን ንቅናቄ ለመፍጠር ያግዛል። በተቋሙና በባለደርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የዘርፉን ችግሮች ለመከላከል መሰረት የሚጥል መሆኑን ዋና እንባ ጠባቂው ዶክተር እንዳለ ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ '' 'የዴሞክራሲ ተቋማት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለመልካም አስተዳደር'፣  'ሰላም ለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር' '' በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ ፅሁፎች ለውይይት ይቀርባሉ ተብሏል። ከዚህም ሌላ በታዋቂ ሰዎች አማካኝነት ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ አነቃቂ ንግግሮች ይቀርባሉ። በተለይ በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል በተሰናዳው በዓል ላይ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤዎች፣ የህግ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች ይታደማሉ። በተጨማሪም ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ሌሎች ባለደረሻ አካላት በበዓሉ ይገኛሉ ተብሏል። በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመከላከል የዜጎችን መብት በአግባቡ ማስከበር ይቻል ዘንድ አስፈላጊውን ግንዛቤ ለመፍጠርና የሚመለከታቸው አካላትም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማሳሰብ ቀኑ በየዓመቱ እንዲከበር ይደረጋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም