የቡና ጥራት ውድድር በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

103
ጥቅምት 11 / 2012 ዓም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡና ጥራት ውድድር ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከአሜሪካ ተራድኦ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ ጋር በመሆን በዓለም ታዋቂ የሆነውን “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” የተሰኘ የቡና ጥራት ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያካሂዳል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎች በመምረጥ ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር በጥራታቸው የላቁትን በተሻለ ዋጋ በጨረታ ለመሸጥና ልዩ ለሆኑ ቡናዎች በዓለም ገበያ ዕድል ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት፤ ውድድሩ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ ብሎም እስካሁን ያልታዩ የቡና ዝርያዎች ጎልተው እንዲወጡ ያስችላል። በቡና ዘርፍ ለተሰማሩ በተለይም ለአርሶአደሮችና አልሚዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ለአገሪቱ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ብለዋል። በውድድሩ በኢትዮጵያ ቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኙ የቡና አምራቾችና አቀነባባሪዎች፣ ላኪዎች፣ ህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎችም በዘርፉ የተሰማሩ ቡና አቅራቢዎች መሳተፍ እንደሚችሉም ገልጸዋል። ለውድድሩ የሚሆኑ የቡና ናሙናዎችን መቀበያ ማዕከላት በጅማ፣ ሃዋሳና ድሬዳዋ ከተሞች የተዘጋጁ ሲሆን  የመጨረሻው ዓለም አቀፍ ውድድርም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል። በአገር ውስጥ ባሉና ከዚህ ቀደም በመላው ዓለም የተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የዳኙ ልምድና ዕውቅና ያላቸው የቡና ገዢዎች ይዳኛል። የጥራት ውድድሩ ለቡና ገዢዎች የበለጠ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎች ለመግዛት እንደሚረዳም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። "ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ" የአምራቾችን ጥቅም ለማስከበር እንደሚሰራና እንደሚያበረታታም ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ውድድሮች አሸናፊ ሆነው የተሸጡ ቡናዎች በተደጋጋሚ የዓለም የቡና ዋጋ ክብረወሰን ሰብረዋል። በውድድሩ የሚሳተፉ አካላት ከጥር 25 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም የቡና ናሙናዎችን ማስገባት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል። አገራዊ የውድድር መድረኩ ከመጋቢት 21 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኩ ደግሞ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል። በውድድሩ ከ40 በላይ የቡና መገኛ የዓለም አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች በዳኝነት ይሳተፋሉ። የቡና ጥራት ውድድር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 በብራዚል የተጀመረ ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት በ11 ቡና አምራች አገራት ተካሂዷል። ከእነዚህም ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ፔሩ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ኮስታሪካ፣ ኒካራጓ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ሜክሲኮ፣ ቡሩንዲ እና ሩዋንዳ ተጠቃሽ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም